በኮንታ ዞን የአመያ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ መምጣቱን ታካሚዎች ገለፁ

የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማሳለጥ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ሆስፒታሉ አስታውቋል።

በአመያ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት ሲያገኙ አግኝተን ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል ወ/ሮ ወይኒቱ ወጁ፣ አቶ አዴመ አሸቶ እና ወጣት ጎምኦለ ጎደቶ እንደተናገሩት፤ በህክምና ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

በህክምና ባለሙያዎች በተለይ በጠና የታመሙ ግለሰቦችንና ወላድ እናቶችን ለማዳን የሚያደርጉት ርብርብ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የሚሰጠው የአምቡላንስ አገልግሎት መቀነሱንና ከጤና መድህን ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ክፍተቶች መቀረፍ እንዳለባቸው ተገልጋዮች አንስተዋል።

የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ አቅደው አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆናቸው በሆስፒታሉ የእናቶችና ሕፃናት ክፍል ባለሙያ አቶ ገሠሠ ገብሬ ተናግረዋል።

የአመያ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ አሻ በበኩለቸው፤ በሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት እየተስተካከለ መምጣቱን ገልፀው፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንና ከነዚህም ውስጥ በተቋሙ የሰለጠነ የሰው ሀይል የማሟላት ሥራ ቀዳሚ ተግባር ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ወደ ሌላ አካባቢ ሪፈር የሚደረገውን ለማስቀረት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሆስፒታሉ 4 ስፔሻሊስቶችና 6 ከፍተኛ ባለሙያዎችን መቅጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ የሚስተዋለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ ከታርጫ ደም ባንክ ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑን አቶ አለማየሁ አብራርተዋል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም እናቶች በጤና ተቋም በመውለድ የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ጤና የመጠበቅ ልምዱ ዝቅተኛ ቢሆንም አሁን ላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በማደጉ ከበፊቱ በላቀ ደረጃ በሆስፒታል እንደሚገለገሉ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ የተቀላጠፈ እንዲሆን ከሆስፒታሉ ጋር በመቀራረብና በመደጋገፍ እየተሰራ መሆኑን በአማያ ከተማ አስተዳደር የጤና ዩኒት ተወካይ ወ/ሮ ቀለሟ መሀሙድ ገልጸዋል።

በኮንታ ዞን የአመያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተመስገን ደጀኔ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ አልፎ አልፎ የመድኃኒት እጥረት እንዳለ በማነሳቱ ችግሩን ይቀርፋል የተባለውን የህዝብ መድኃኒት ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአመያ ከተማ ማቋቋም መቻሉን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን