መምሪያው በጌዴኡፋ ቋንቋ የመጀመሪያ የሆነውን የሰዋሰው መጽሐፍ አዘገጃጀት ዙሪያ ከዘርፉ ምሁራን ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ፣ የጌዴኡፋ ቋንቋ ለ31 ዓመታት የትምህርትና የሥራ ቋንቋ ሆኖ ቢቆይም የተደራጀና በቂ የሰዋሰው መጽሐፍ ባለመኖሩ በቋንቋ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የጌዴኦ ብሄር ባህል እና ቋንቋ ለማሳደግ በዞኑ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የቋንቋ እና ባህል ክበባትን በማቋቋም እና በመደገፍ የበኩሉን እየተወጣ እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው፤ በቋንቋው የሰለጠኑ እና ብቁ መምህራንን ለመፍጠር በመምህራን አቅም ግንባታ ላይም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቋንቋውን የሳይንስ እና የጥናት ቋንቋ ለማድረግ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን ከማዘጋጀት ረገድ የተቋማት እና የምሁራን ሚና የጎላ መሆኑን በመጠቆም የዞኑ ትምህርት መምሪያ የመጀመሪያ የሆነውን የጌዴኡፋ ቋንቋ የሰዋሰው መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለማሳተም የመጀመሪያ ምዕራፍ በማጠናቀቅ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዲላ ትምህርት ኮሌጅ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግምገማ ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በዲላ ዩኒቨርስቲ ጌዴኡፋ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ፍቃዱ ንጉሴና የዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ ተረፈ ሾንጦ በመጽሐፍ አዘገጃጀት ዙሪያ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።
በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳባቸውን የሰጡት የዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን አቶ ተረፈ ሾንጦ፣ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጉዳዮችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መታረም ያለበትን ጉዳይ በማረም በአጭር ጊዜ መጽሐፉ ታትሞ በዞኑ ከሚከበረው ዳራሮ በዓል ቀደም ተብሎ በሚዘጋጀው በጌዴኡፋ ቋንቋ ሲምፖዚየም ለማድረስ በትኩረት እንደሚሠራም አሳስበዋል።
መምህር ጌታቸው ፀጋዬ እና ደሣለኝ በቀለ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የጌዴኡፋ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ መምህራን እና የመድረኩ ተሳታፊዎች ሲሆኑ፣ ቋንቋውን ማሳደግ የሚቻለው ከንግግር ባሻገር የተለያዩ ሥነ ጽሑፍ በማሳተም እና በማንበብ መሆኑን በመጠቆም ቋንቋውን ለማሳደግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄን ለመመለስ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን በጎፋ ዞን ቡልቂ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በኮሌጁ እየተሰሩ ያሉ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ የፈጠራ ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
የየም ብሔረሰብ ሀገር በቀል የመድሃኒት ለቀማና ቅመማን በጥናት በመደገፍ ሰንዶ ለማስቀመጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።