የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ በትምህርት ጥራትና ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋዕጾ እንዳለው ተጠቆመ

የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ በትምህርት ጥራትና ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋዕጾ እንዳለው ተጠቆመ

ሀዋሳ: ጥር 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተጀመረው የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ መርሐ-ግብር በትምህርት ጥራትና ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋዕጾ እንዳለው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንደ ሀገር በቅድመ አንደኛ ደረጃ ላይ ያለው ክፍተት መለየቱን ጠቁመው፥ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለተለየው ችግር መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ በ11 ወረዳዎች ሲሰጥ የነበረውን የምገባ መርሐ ግብር፥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተማሪዎች ምገባ ቁጥርን በ10 ሺዎች በማሳደግ አሁን ላይ ከ65 በላይ ትምህርት ቤቶች ከቅድመ አንደኛ እስከ አንደኛ ደረጃ ምገባ መጀመሩን ገልጸዋል።

አንደኛው የትምህርት ጥራትን ሊያሻሽል የሚችለው የትምህርት ቤት ምገባ ነው ያሉት አቶ አንተነህ፥ አንዳንድ ቤት ቁርስ እንኳ በአግባቡ የማያገኙ ተማሪዎች መኖራቸውን አንስተዉ፥ ነገር ግን ተማሪ እየተራበ መምህር የሚለውን ሊሰማና ትንተና ሊሰራ አይችልም ብለዋል። የትምህርት ቤት ምገባ በትምህርት ጥራት ላይ እና በተማሪ ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋእጾ እንዳለው አስረድተዋል።

የምገባ መርሐ ግብር መጀመሩ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የተለያዩ አካባቢ መምህራኖች ናቸው።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለትምህርት ቤት ምገባ ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ በየትምህርት ቤቱ የተማሪዎች መመገቢያ ክፍሎችን መገንባታቸውን በተለያዩ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ተዘዋውረን ተመልክተናል።

በቅድመ መደበኛ ትምህርት ከዚህ ቀደም ያላዩትን በማየታቸው መደሰታቸውን የገለጹት መምህራኖቹ፥ የለውጡ መንግስት እንዲህ አይነት ለትውልድ የሚጠቅም ሰዉ ተኮር ተግባር እዉን ማድረጉ ያስመሰግነዋል ብለዋል።

የቅድመ መደበኛ የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት መጀመሩ ከዚህ በፊት ያጋጥም የነበረውን የህፃናት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ አልፎ አልፎ መምጣትና የማርፈድ ምጣኔ መቅረፉንና ተማሪዎች በአካልና በአእምሮ ንቁ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉን መምህራኑ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በዘርፉ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የትምህርት ቤት ምገባ ለተማሪዎች ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ነው።

የቅድመ መደበኛ ምገባ መርሐ ግብር ተማሪዎች በትምህርታቸው ንቁ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፥ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልና የገበያ ትስስር መፍጠሩ ተመላክቷል።

የትምህርት ቤት የምገባ መርሐ ግብር መኖሩ እንዳስደሰታቸዉ የሚናገሩት በምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ ነዋሪ አቶ ሸረፋ ቡዜር፥ ልጆቹን የሚያበሏቸው ነገር ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት እንደማይልኳቸው ጠቁመው፥ አሁን ግን እድሜ ለመንግስት ልጆቹን ተቀብሎ አብልቶ እያስተማረ በመሆኑ፥ ምን ላብላቸው ከሚል ሰቀቀን እንደታደጋቸው ተናግረዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው ሸምሲያ ሰዒድ አሊ፥ በአሁኑ ወቅት ባለቤቷ ከጎኗ ባለመኖሩ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ በምታገኛት አነስተኛ ገቢ ልጆቿን ታስተምራለች።

ልጆቿ በትምህርት ቤቱ በሚያገኙት የምገባ መርሐ ግብር ደስተኛ መሆኗን ጠቁማ፥ እሷም በየቀኑ ለልጆቿ ቁርስ ዳቦ ለመግዛት ታወጣ የነበረውን ወጪ የቀነሰላት መሆኑን ገልጻለች።

የመርሃ ግብሩ ተግባራዊ መሆን ወላጆች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ለመመልከት ችለናል።

በቅድመ መደበኛ ትምህርት የምገባ መርሃ-ግብር መጀመሩ የወላጆችን ጫና ከማቃለሉ ባሻገር፥ ህፃናት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ፍላጎታቸውን እንዲጨምርና በትምህርት ቤት ቆይታቸዉ ተረጋግተው እንዲከታተሉ በማድረግ ለትምርት ጥራት መሳካት መሠረት የሚጥል መሆኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ