በምርት ዘመኑ የሽምብራ ሰብል በማምረት ተጠቀሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ
በምርት ዘመኑ የፀደይ ወራት የሽምብራ ሰብል በማምረት ተጠቀሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ገልጸዋል።
በልዩ ወረዳው 7 ሺ 6 መቶ ሄክታር መሬት በሽምብራ ሰብል መሸፈኑን የልዩ ወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።
አርሶ አደር ሸምሱ ኡመር፣ መሀመድ ሞሳና ሙባሪክ ሀዲ የቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡
የምርት ዘመኑ የበቆሎና የጤፍ ሰብሎችን የመሰብሰብ ስራ በማጠናቀቅ በፀደይ ወራት በመሬቱ ላይ የሽምብራ ሰብል በማምረት ምርታማነታቸውንና ተጠቀሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሰብሉን የመንከባከብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ መሬታቸው ለሽምብራ መሬት ምቹና ተስማሚ በመሆኑ ምርታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
በተለይም በፀደይ ወራት በሽምብራ የተሸፈነ ማሳ ለበልግ እርሻ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ መሀመድአሚን ሸምሱ በልዩ ወረዳው የፈረጀቴ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ ሲሆኑ የቀበሌው አርሶአደር የበቆሎና የጤፍ ሰብል የመሰብሰብ ስራ በማጠናቀቅ በማሳው ላይ ሽምብራ እንዲያመርት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በመሰራቱ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ለአርሶ አደሩ በቅርበት ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውንም በመጠቆም፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል እንደገለፁት በምርት ዘመኑ በፀደይ ወራት 7ሺ 6 መቶ ሄክታር መሬት ሽምብራ ለምቷል።
በተለይም በልዩ ወረዳው በፀደይ ወራት ሽምብራ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የሽምብራ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አብድልሽኩር አርሶ አደሩ ሰብሉን የመንከባከብና የመከታተል ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ