በፍትህ ተቋማት እና በትራንስፖርት ዘርፍ የወጡ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ገለፁ
ቋሟ ኮሚቴዎቹ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የባለፈውን ግማሽ አመት እቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ነጋሽ እንዳሉት፤ የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ለሴቶች፣ ህፃናት እና ልዩ የህግ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች እየተደረገ ያለው እገዛ የሚበረታታ ነው።
ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ ከዘመናዊ የፍትህ አሰራር ጋር በማጣመር እየተሰራበት ያለው ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ነፃ ጥብቅና የሚሰጣቸው ሰዎች በአግባቡ ጠበቃ የመቅጠር እቅም እንደሌላቸው በመለየት በኩል ያለው ክፍተት ለመድፈን ሊተኮርበት እንደሚገባም አቶ ጌታሁን አመላክተዋል።
የዞኑ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑርአህመድ አለዊ እና የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓለምይርጋ ወልዴ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ መናኸሪያዎች ለሊት ይወጡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በማስቆም ህዝቡ ከአውሬ እና ከእንግልት መገላገል መቻሉ አድንቀዋል።
የነዳጅ ግብይት ስርዓት ላይ የሚስተዋለው ችግር ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን በማስተካከል ተገልጋዩ ካላስፈላጊ ወጪ ማዳን እንደሚገባም አንስተዋል።
የትራንስፖርት ክፍያ ታሪፍ ይፋ ከማድረግ ባለፈ ተሳፋሪን አስገድደው ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎች እና ለህጉ አጋዥ ያልሆኑ ተሳፋሪዎች ስርዓት እንዲይዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የወጡ ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑም በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ሀላፊ አቶ ኤልያስ ሰብለጋ በበኩላቸው በዞኑ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የመርማሪ ፖሊስ እጥረት፣ የአንዳንድ ፖሊስ የስነ ምግባር ጉድለት፣ የውስን ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት ህብረተሰቡ ሙስና ለማጋለጥ ያለው ተነሳሽነት መቀነስ እና የምስክርነት ቃል በመስጠት በኩል የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ምድብ ችሎት አለመኖር ሀላባ ድረስ ባለጉዳዮች ለመንቀሳቀስ በሚወስድባቸው ጊዜና ገንዘብ የተነሳ ፍትህ ለማግኘት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አመላክተዋል።
የጉራጌ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ በተጠናቀቀው ግማሽ አመት 21 የትራፊክ አደጋ መድረሱን እና ከ4 ሚልዮን በላይ የንብረት ውድመት ማጋጠሙን ገልጸዋል።
የወልቂጤ፣ የአረቅጥ እና የዳርጌ መናኸሪያዎች ሳቢና ምቹ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ከአጎራባች አካባቢዎች በተለይም ከአሮሚያ ክልል ከወሊሶ አስከ ሰበታ ክፍለ ከተማ ጋር በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታት በተሰራው ስራ መልካም ውጤት ተገኝቷል ብለዋል ወ/ሮ ትብለጥ።
የተጀመሩ የድልድይ እና መንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት ተመዝግበዋል ብለዋል።
ከአዲስ አበባ መናኸሪያ – መሃልአምባ – አረዳ እንዲሁም አረቅጥ – ባድ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት ቢደረግም እስካሁን ለማሳካት አለመቻሉን ተናግረዋል።
በእለቱም የዞኑን ፖሊስ መምሪያ እና የሌሎችም ተቋማት የተጠናቀቀውን ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ተገምግሟል።
ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/