በቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሩና የተደራጁ ወጣቶችን በመስኖ ልማት ስራ በማሰማራት በዘርፉ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ አርሶ አደሩና የተደራጁ ወጣቶችን በመስኖ ልማት ስራ በማሰማራት በዘርፉ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የልዩ ወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት ገለፀ።
በልዩ ወረዳው በምርት ዘመኑ ከ2 ሺህ 6 መቶ ሄክታር በላይ መሬት በ1ኛ ዙር መስኖ መልማቱም ተጠቁሟል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል በወረዳው በምርት ዘመኑ የመስኖ ልማት ስራ 2 ሺ 6 መቶ 56 ሄክታር መሬት በ1ኛ ዙር መስኖ መልማቱን አስታውቀዋል፡፡
የዘር ሽንኩርት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ ቲማቲምና ጎመን በመስኖ ልማት እየለሙ ከሚገኙ ሰብሎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንና በተለይም የዘር ሽንኩርት በክላስተር በስፋት በማምረት ከዚህ ቀደም ከሌሎች አካባቢዎች ይመጣ የነበረውን የዘር አቅርቦት በልዩ ወረዳው ለመሸፈን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ልዩ ወረዳው ለመስኖ ልማት ስራ ምቹ ቢሆንም የዘመናዊ መስኖ ልማት አውታሮች ውስንነት በመኖሩ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የተለያዩ የውሃ አማራጮች፣ የሰው ሃይል፣ የመሬትና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በመስኖ ልማት ስራ የአርሶ አደሩንና በዘርፉ የተደራጁ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም አስፈላጊውን ግብዓት የማቅረብና የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ሃላፊው፤ አርሶ አደሩ ዝናብን ጠብቆ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ከማምረት ተላቆ በመስኖ በአመት ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ ማምረት እንዲችል እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልፀው አርሶ አደሩ የምግብ ፍጆታውን በመሸፈንና ለገበያ በማቅረብ የወቅቱን የገቢያ ሁኔታንና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የመስኖ ልማት ስራ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩና የተደራጁ ወጣቶች እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በመስኖ ልማት ስራ እንዲሰማሩ በተደረገው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የገለፁት ደግሞ በልዩ ወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት የሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀይሉ ገብሬ ናቸው፡፡
የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የባለሙያ የቅርብ ድጋፍና ክትትል አየተደረገላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
አርሶ አደር ጅላሉ ኑሮ በልዩ ወረዳዉ ፈረጀቴ ቀበሌ በ5 ሄክታር መሬት የዘር ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ የጎሮ አትክልቶችን በማልማት ላይ መሆኑንና በዚህም ለስራ አጥ ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስረድቷል፡፡
ሌላኛው አርሶ አደር አህመድ አባተ በልዩ ወረዳው የሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ለበርካታ አመታት በሳዉዲ አረቢያ በስደት መቆየቱን አስታውሶ የመስኖ ልማት ስራ በመሰማራት በራስ ሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ያስረዳል፡፡
በዘርፉ ያላቸው ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የገለፁት አርሶ አደሮቹ ግብዓትን በወቅቱ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡
በዘርፉ በቋሚነትና በጊዜያዊነት በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/