የሥራ ባህልን በማጠናከር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታት እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ ገለፁ
በሰው መነገድ እና ድንበር የማሻገር ወንጀል ዙሪያ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በሀዲያ ዞን ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ አዘጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
የዞኑ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሴ አውዶ ባደረጉት ንግግር፤ የሰው ልጅ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማሕበራዊ ፍላጎቶችን ለማጣጣም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ግድ ቢሆንም እንቅስቃሴው ሕግን ባልተከተለ መልኩ ሲሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን እንደሆነ ተናግረዋል።
የመብት ጥሰቶች መፈጸም፣ የሕይወት ዋጋ መክፈል፣ ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መፈጠር እና ሌሎችም መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ጥቂቶቹ እንደሆኑ የገለጹት ሀላፊው መንግስት ችግሩን ለመቀነስ በተቀናጀ መልኩ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመድረኩ በመገኘት ”መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጽዕኖ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተማራማሪ ዶ/ር ፀደቀ ለምቦሬ ስለ ስደት አሉታዊ እና አዎንታዊ ገጽታ በስፋት አስረድተዋል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ስደት የተማሩ ሰዎች ክህሎት በማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከራሳቸው አልፎ አገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚረዳ ሲሆን ለጉልበት ስራ ወደ ተለያዩ አገራት በሚሰደዱ ላይ ግን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፍላል።
መንግስት ዜጎችን ከእንደዚህ አይነት እንግልት ለመታደግ በቂ የስራ ዕድል በስፋት ማመቻቸት እንዳለበት ዶ/ር ፀደቀ መክረዋል።
የቀረበውን ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻ በማድረግ አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ለወጣቶች ፍትሐዊ የሥራ ዕድል አለመፈጠርና ወጣቶችን ያሳተፈ ተግባራትን አለመፈጸም ሕገወጥ ስደት እንዲበረከት ማድረጉን አንስተው ወጣቱን ታሳቢ ያደረጉ የስራ ዕድሎች መፈጠር እንደለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ በዞኑ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል ቢፈጠርም በወጣቶቹ ስራ የማማረጥ ዝንባሌ መኖር እና በአገራቸው ሰርቶ የመለወጥ ፍላጎት እምብዛም አለመኖር ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ እንደሆነ አስረድተዋል።
ዜጎች በአገራቸው ሰርቶ መለወጥ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ተጨባጭ ተሞክሮዎች ስለመኖራቸው
ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ የሥራ ባህልን በማጠናከር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መግታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዕለቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የዕድር ጥምረቶች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች እና በየደረጃ የሚገኙ የመንግስት ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን የስደት አስከፊነት የሚገልጽ ጭውውት ቀርቧል።
ዘጋቢ፡ ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/