አመራሩ በቀጣዮቹ 6 ወራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለቅሞ መፍታት እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰዉ(ዶ/ር) አሳሰቡ
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደዉ 22ኛ መደበኛ ጉባኤ የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
ለ2 ቀናት በሆሳዕና ከተማ በተካሄደዉ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት 22ኛ መደበኛ ጉባኤ፤ የክልሉ አስፈፃሚ አካላት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደርጎበታል።
በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ፤ በዕቅድ ላይ በቂ ዝግጅት በማድረግ አዳዲስ ሀሳቦች እንዲካተቱ መደረጉ በጥንካሬ የሚታይ መሆኑን የገለፁት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ(ዶ/ር)፣ በፈፃሚ ዝግጅት ላይ የነበረዉ ተግባርም በጥንካሬ የሚወሰድ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በተግባር ምዕራፍ ስራን ቆጥሮ መዉሰድ፣ ዉጤትን እየገመገሙ መሄድ፣ ጊዜን ለስራ ብቻ ማዋል እንዲሁም የህዝብን ተጠቃሚነት እየገመገሙ ተሳትፎን ማሳደግ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
አመራሩ ከደባል አጀንዳ በመዉጣት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ መፍታት የቀጣይ 6 ወራት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን በማጠቃለያ ሀሳባቸዉ ያሳሰቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ አገልግሎትን ከእጅ መንሻ በፀዳ መልኩ በስታንዳርድ መስጠት ይገባል ብለዋል።
በከተሞች የማህበር ቤት ግንባታን ወደ ስራ ማስገባት፣ የወጣቶችና ሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ዉድነትን ማረጋጋት የቀጣይ 6 ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የገቢና ስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችም በቀሪ ወራት በትኩረት መመራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለባቸዉ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቀሩ ተግባራትም እልባት ማግኘት እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ዘጋቢ፡ ድልነሳው ታደሰ
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/