በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰራ ቅንጅታዊ ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል – የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰራ ቅንጅታዊ ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል – የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ

ሀዋሳ፡ ጥር 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰራ ቅንጅታዊ ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት ባከናወናቸው ጉዳዮች እና በተመዘገቡ ለውጦች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በሰጡት መግለጫ እንደ መንግስት ለመፍታት ከተቀመጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የዜጎች የስራ አጥነት ችግር አንዱ ነው።

በተለይም ዘላቂ የስራ እድል ለመፍጠርና የስራ አጥነት ችግርን በልዩ ትኩረት ለመፍታት መሰራቱን ተናግረዋል።

የስራ ፈላጊ ዜጎች ቁጥርን ታሳቢ በማድረግ በአዲስ እይታ በሰፊው ማቀድ፣ ፍጥነትና ጥራትን አክሎ በሰፊው መስራት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ በመደረሱ ከኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር አዳዲስ የስራ እድል ፈጠራ እሳቤዎች መምጣታቸውንም አስረድተዋል።

በመሆኑም የስራ እድል ፈጠራ ሲታሰብ ከእለት ጉርስ በላይ በመሆኑ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ጋር አስተሳስሮ መስራት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ሃላፊው፤ የብዝሃ ዘርፍ ሴክተሮች ስራ እየፈጠሩ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ግኝት ዜጎች ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ማድረግ እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ መወሰዱንም ነው አቶ ሙስጠፋ ያብራሩት።

በዚህም በሁሉም ዘርፎች ያሉ እድሎችን አሟጦ በመጠቀም ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረጉ ተግባር በተጠናከረ መልኩ እየተሰራበት እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ነው ያሉት።

ወደ ስራ የሚሰማሩ ዜጎች የሚሰሩት ስራ በክህሎትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል ወደ ስራ ከመሰማራታቸው በፊት በቂ ስልጠና እየተሰጠ በማሰማራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ሀላፊው ተናግረዋል።

ዜጎች በሚሰማሩበት ስራ ላይ ከራሳቸው ባለፈ ለሃገር ኢኮኖሚ አበርክቷቸው ከፍ እንዲል ታሳቢ ያደረገ ተግባር እየተከናወነ እንዳለና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አመላክተዋል።

በባለፉት 3 አመታት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሰለጠኑ እና የተሻሉ በህጋዊ መንገድ የውጭ የስራ እድል ሃገርን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች ማሰማራት መቻሉንም በማሳያነት አንስተዋል።

ባለፈው አመት ክልሉን ከማደራጀት ስራ ጎን ለጎን በተሰራ ጠንካራ ሥራ 175 ሺህ ስራ አጥ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ሲሉም አክለዋል።

በተያዘው የ2017 በጀት አመት ለ350 ሺህ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፈው ግማሽ አመት ከ295 ሺህ በላይ ስራ አጥ ዜጎች ወደ ስራ የተሰማሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 19 ሺህ 332 የሚሆኑት የውጭ ሀገር የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።

በቀጣይ በዘርፉ ዘላቂነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ በመጥቀስ ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ሀላፊው አቶ ሙስጠፋ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን