በአካባቢው የሚዘወተሩ ስፖርቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን ብቁ አሰልጣኞችን ለማፍራት እየሰራ እንደሚገኝ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ

በአካባቢው የሚዘወተሩ ስፖርቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን ብቁ አሰልጣኞችን ለማፍራት እየሰራ እንደሚገኝ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአንደኛ ደረጃ የቅርጫት ኳስ የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚዘወተሩ ስፖርቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን ብቁ አሰልጣኞችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ ገልጸዋል።

በክልሉ በስፋት ከሚዘወተሩና በውድድሮችም አመርቂ ውጤት ከሚመዘገብባቸው ስፖርቶች መካከል ቅርጫት ኳስ ቀዳሚው መሆኑን ያነሱት አቶ ሰይፈ፤ ይህንን አቅም በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ስልጠናው ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በአካልና አዕምሮ የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት የስፖርት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እሸቱ ተሾመ ናቸው።

የቅርጫት ኳስ ስፖርት በክልሉ ከቀድሞ ጀምሮ ህብረተሰቡ ይጫወተው እና ይዝናናበት እንደነበር አንስተው ስልጠናው ወልቂጤ ላይ ሲደረግ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ስልጠናው በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን በስፖርቱ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የተዘጋጀ እንደነበር ያነሱት ደግሞ የቢሮው የስፖርት ስልጠና ክፍል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍሬው ጌቱ ሲሆኑ በቀጣይ ሰልጣኞች በስልጠናው የጨበጡትን እውቀት በተግባር እንዲያውሉት የክትትል ስራዎች እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ታዳጊዎችን በሰለጠኑ አሰልጣኞች ማሰልጠን ልጆች በስነ-ምግባር ታንጸው በስፖርት ክህሎት ዳብረው እንዲያድጉ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት የስልጠናው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዘመዴ በቀለ ናቸው።

አንድ አሰልጣኝ በእውቀትና በቴክኒክ ሲያሰለጥን ቡድኑ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል እና ስልጠናው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ የታገዝ እንደነበር ያነሱት ኢንስትራክተር ዘመዴ፤ በመጨረሻም ሰልጣኞች የስልጠና መለኪያ ፈተና በመውሰድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

መሰል ስልጠናዎች መዘጋጀታቸው የአሰልጠኞችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለቅርጫት ኳስ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ስልጠናው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ የታገዘ መሆኑ አመቺ እንዳደረገው ያነሱት ተሳታፊዎቹ፤ በቀጣይ በአካባቢያቸው ስፖርቱን ለማሳደግ ተተኪዎች ላይ በመስራት ውጤት እንደሚያመጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን