የጉራጌ ዞን ሰላም እና ፀጥታን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ቢሆንም አጥፊዎች ተጠያቂ በማድረግ በኩል ይበልጥ መሰራት እንዳለበት የዞኑ ምክር ቤት አስገነዘበ

የጉራጌ ዞን ሰላም እና ፀጥታን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ቢሆንም አጥፊዎች ተጠያቂ በማድረግ በኩል ይበልጥ መሰራት እንዳለበት የዞኑ ምክር ቤት አስገነዘበ

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የባለፈው ግማሽ ዓመት የየመስሪያ ቤቶችን አፈፃፀም እየገመገሙ ነው።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ሰላም እና ፀጥታ፣ ከተማ ልማት፣ ሚሊሻ፣ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና፣ ደንና አካባቢ ጥበቃ፣ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊዎች እና ስራ አመራር አካላት በተገኙበት አፈፃፀማቸውን ገምግሟል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ነጋሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሰላምና ፀጥታ፣ ፖሊስ እንዲሁም ሚሊሻ ይበልጥ ተቀናጅተው በመስራት የዞኑ መረጋጋት እና ህዝባችን ለሚፈልገው በሰላም ተንቀሳቅሶ የመኖር ሰብአዊ መብት ማረጋገጥ ይገባል።

ወልቂጤ፣ አበሽጌ እና ቆሴ የብጥብጥ አካባቢ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ዘራፊ እና ፅንፈኛ አካላትን ለመግታት ዞኑ ከክልሉ እና ከፌደራል አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል።

አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ግጭት ለማባባስ እና ችግሩ እንዳይፈታ እየሰሩ በመሆኑ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።

ሌላኛው የዘርፉ ቋሚ ከሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ከድቻ ተማም እና ወ/ሮ አርሺያ አህመድ በሃይማኖት ተቋማት እና በአማኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እየተፈቱ ያለበት መንገድ አስተማሪ በመሆኑ ልምዱን በመቀመር ማስፋት ይገባል ብለዋል።

በወልቂጤ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የሚያደናቅፉ አካላት ተገቢነት ከሌለው እንቅስቃሴያቸው ለማስቆም ከህዝብ እና ከመንግሥት የሚታየው ትእግስት የሚበረታታ በመሆኑ ስራው መስተጓጎል እንደሌለበት ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ የህያ ሱልጣን፤ ወጣቶችን የሚጎዱ ቁማር ቤቶች እና ለወንጀል ምቹ የነበሩ ጭፈራ ቤቶች ላይ ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።

ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርና ሽያጭ እንዲሁም ዝርፊያ ላይ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእኖር ኤነር መገር ወረዳ ቆሴና ዙርያው፣ በአበሽጌ ወረዳ እና በወልቂጤ ከተማና ዙሪያው የተስተዋለው የፀጥታ ችግር ለመፍታት በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።

አሁንም በህግ ቁጥጥር ስር ያልዋሉ አጥፊ ቡድኖች እና ግለሰቦች በመኖራቸው የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመግታት አዳጋች አድርጎታል ብለዋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ወንጀለኞችን አጋልጦ መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

ፅንፈኞች በፈጠሩት የፀጥታ ችግር የተነሳ በአበሽጌ ተፈናቅለው የነበሩ 5 ሺ 600 ሰዎች አካባቢውን ሰላማዊ በማድረግ ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል ሲሉም አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን