በተያዘው 2017 በጀት አመት አጋማሽ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ግብር መሰብሰብ መቻሉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

በተያዘው 2017 በጀት አመት አጋማሽ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ግብር መሰብሰብ መቻሉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

ግብር ለሀገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት መፋጠን ዋነኛ መሰረት እንደመሆኑ እንደ ሀገር በዘርፉ የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ የገቢ አቅምን ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ዞኑ የሚያመነጨውን የገቢ አቅም በተገቢው ለመሰብሰብ በተደረገው እንቅስቃሴ በተያዘው 2017 በጀት አመት ባለፉት 6 ወራት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤቶች በአጠቃላይ ከ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢሊየን 213 ሚሊዮን 826 ሺ ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 76 ነጥብ 5 ከመቶ ማሳካት መቻሉን የገለፁት የስልጤ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር አለሙ ናቸው።

በዘርፉ የተደረገውን የግብር ማሻሻያ ተከትሎ የአመቱን ጥቅል ገቢ በላቀ ሁኔታ ለመፈጸም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ከድር ጠቁመዋል።

የገጠር መሬት ገቢ አሰባሰብን ጨምሮ ከአዲሱ የግብር ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በተሳሳተ መልኩ የሚነሱ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በተለያዩ አማራጮች እየተሰጠ መሆኑንም ኃላፊው አብራርተዋል።

አዲሱ የግብር ማሻሻያ መንግስት ሀገራዊ የገቢ አቅምን ለማጎልበት ጥናትን መሰረት አድርጎ ወደ ትግበራ እንዲገባ የተደረገ ስለመሆኑም አቶ ከድር አመላክተዋል።

በዞኑ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን የተጀመረው የአሰራር የማሻሻያ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ግንባር ቀደም ሞዴል ግብር ከፋዮችን ከዞን እስከ ክልል እውቅና በመስጠት የማበረታታት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በተሰማራበት የንግድ ዘርፍ የደረሰኝ አጠቃቀምን በማዘመን፣ ከሸማቾች ጋር ፍትሐዊ የንግድ መስተጋብር ማድረግ እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ከድር፤ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግብር በተገቢው በመክፈል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: አብዱልሃሚድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን