በሆሳዕና ከተማ ወጣቶች  ለኮሪደር ልማት ስራ የሚውሉ የግንባታ ምርቶችን በማቅረብ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ተባለ

በሆሳዕና ከተማ ወጣቶች  ለኮሪደር ልማት ስራ የሚውሉ የግንባታ ምርቶችን በማቅረብ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ተባለ

በተለያዩ ኢንተርፕራይዝ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለኮሪደር ልማት ስራ የሚውሉ የግንባታ ምርቶችን በማቅረብ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን  የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት አመላክቷል።

ስራ ሳይንቁ በመስራታቸው የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን አንዳንድ በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶች ተናግረዋል።

በከተማው ውሃ ለልማት ብሎኬትና ቴራዞን ኢንተርፕራይዝ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት በለጠ ደገፈ ማህበሩ በ3ሚሊየን ብር ከፒታልና በ5 ወጣቶች ወደ ስራ የገባ ሲሆን በቀን አስከ 200 ካሬ የሚደርስ ቴራዞን እና ባርካታ ብሎኬቶችን እያመረተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።ለሆሳዕና ከተማ ኮርደር ልማት ስራ ቴራዞን በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ የማህበሩ ከፒታል ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን እና ለ45 ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን የገለጸው ወጣት በለጠ በቀጣይ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገ የተሻለ ስራ ለመስራት መታቀዱንም ተናግሯል።

ሌለኛው የጎዳንቾ የችግኝ ጣቢያ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ጌታቸው ዘውዴ በበኩሉ በ2016 ዓ/ም በ2መቶ10 ሺህ ብር መነሻ  ካፒታል የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን የማፍላትና የማዳቀል ስራ ላይ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ  ከ15 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንና  ከ1ሚሊየን በላይ ካፒታል ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

ለስራ ቦታው በዓመት 120ሺህ ኪራይ እንደሚከፈል የጠቆመው ወጣት ጌታቸው ስራውን በማስፋፋት የአካባቢውን አርሶአደር እና የከተማውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በመንግስት በኩል የቦታ አቅርቦት ችግር መፈታት አለበት ብሏል።

ሌሎች ወጣቶችም ስደትን ሳይሆን ስራ ፈጠራን አማራጭ ማድረግ አለባቸው በማለት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር 723 ነባር እና 134 አዲስ  ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ የገለጹት የከተማው የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የስራ ዕድል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ወርቁ ናቸው።

ከ134ቱ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች 88ቱ በባለፉት ስድስት ወራት የተደራጁ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ አስራ አንዱ በቤተሰብ ፓኬጅ የተደራጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እነዚህ በኢንተርፕራይዞች የተደረጁ ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ፣በግብርናው ዘርፍ በዶሮ እና በከብት እርባታ ፣ የፍራፍሬ ችግኝ በማፍላት፣ በቴራዞን እና የግንባታ ግብአቶች በማምረትና በሌሎችም ዘርፎች በመሠማራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ላይ እደሚገኙም አብራርተዋል።

በከተማው በበጀት ዓመቱ 17ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች ተለይተዋል ያሉት አቶ ተመስገን ከ11 ሺህ በላይ ወጣቶች በሀገርና ከሀገር ውስጥ የስራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ብለዋል።

ለአብነትም በከተማው ውሃ ለልማት ብሎኬትና ቴራዞን ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ  ለሆሳዕና ከተማ ኮርደር ልማት ቴራዞን እና ሌሎችንም የግንባታ ምርቶችን በማቅረብ እየተወጣ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ዘርፉን ለማሳደግ ከፈለጉ ከደቡብ ከፒታልና ከልማት ባንክ ብድር ማግኘት እንዲችሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አሳውቀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ለ6 ማህበራት የ17ሚሊዮን ብር ብድር መመቻቸቱን የጠቆሙት አቶ ተመስገን

በኢንተርፕይዞቹ ተገቢ የምክር የስልጠና፣ የብድርና የገበያ ትስስር እየተፈጠረ ነው  ብለዋል።

የመሬት አቅርቦት ችግርን በቅርቡ ለመፍታት የሚያስችል  ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፡ ኤርጡሜ ደንኤል-ከሆሳዕና ጣቢያችን