የጥንት አባቶቻችን ያስቀመጡልን የጀፎረ ቅርስን ጠብቆ በማቆየት ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ተናገሩ
ዋና አስተዳዳሪው “ጀፎረ ዘመንን የቀደመ ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ አሻራ” በሚል የተዘጋጀው የገጠር ኮሪደር ልማት በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ወሽዘውያር ቀበሌ አስጀምረዋል፡፡
የጥንት የጉራጌ አባቶች ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ መገለጫ የሆነው ጀፎረ ጥንታዊ ይዘቱ ተጠብቆና አለም አቀፋዊ ሀብት ሆኖ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሀገራዊ እውቅና የተሰጠው የጀፎረ ባህላዊ ቅርስ የቀደምት የጉራጌ አባቶች ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ምቹነት በማሰብ ያቆዩት ሀብት ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የጀፎረ ይዘት ከትውልደ ወደ ትወልድ እንዲተላለፍ ያስቻለው የሚጠበቅበት ጠንካራ ባህላዊ ስርዓት ስለነበረው እንደሆነ ያነሱት አቶ ላጫ፤ አሁን ላይ ከዚህ ህግ በማፈንገጥ ይዘቱን እንዲቀየር የሚያደርጉ ጥፋቶች ጉራጌን የማይመጥን በመሆኑ መታረም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የእኩልነት ምልክት እና የጋራ ሀብት የሆነው ጀፎረን በጋር መጠበቅ እንደሚስፈልግ አቶ ላጫ አመላክተው፤ እንደ ዞኑ መንግስትም ጀፎረን ዓለም አቀፍ ቅርስ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው፤ ጀፎረ የጉራጌ ማህበረሰብ ሀዘኑም ሆነ ደስታውን የሚያስተናግድበት የሁሉም የጋራ ሀብት ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የገጠር ኮሪደር ልማት ሲጀመር መነሻ የተደረገው የጉራጌ ጀፎረን በመጠበቅና በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑም ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል፡፡
በዞኑ እኖር ወረዳ ወሽዘውያር ቀበሌ ነዋሪ ከሆኑ የእድሜ ባለፀጋ አባቶች መካከል አቶ ታደሰ ዥንገታ እና አቶ ዘርጋ ሽርታጋ እንዳሉት፤ የጥንት አባቶቻቸው ባወረሷቸው የጀፎረ ባህላዊ ቅርስ አሁንም ድረስ ማህበራዊ አገልግሎቶች ይፈፀሙበታል፡፡
የጀፎረን ነባሩን ይዘት የሚቀይሩ ህገ ወጥ ድርጊቶች በማስተካከልም ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚጥሩም ገልፀዋል፡፡
ዞናዊ የገጠር ኮሪደር ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የሀገር ሽማግሌዎች ታድመዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/