በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዓመታት በመሠረተ ልማት ዘርፍ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በየደረጃው በተደረገ ጥረት ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉ ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዓመታት በመሠረተ ልማት ዘርፍ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በየደረጃው በተደረገ ጥረት ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉ ተገለፀ

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በመሠረተ ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት እና በተመዘገቡ ለውጦች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ በሰጡት መግለጫ፤ የክልሉ ህዝብ ከሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መካከል የመሠረተ ልማት ተደራሽነት እና ኢ-ፍትሃዊነት ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ በዘለለም ከዚህ በፊት በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ያለማጠናቀቅ እና የመጓተት ችግሮች እንደነበሩ በማውሳት፤ ይህም በዘርፉ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

ይህንን ተከትሎም በክልሉ በመንገድ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ እና በመስኖ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት በየደረጃው በተደረገ ጥረት ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በተለይም በመንገድ ልማት ዘርፍ በክልሉ ለረጅም ጊዜ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ በርካታ ፕሮጀክቶች እንደነበሩና እነዚህ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትርጉም ባለው መልኩ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ ሌሎች ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም አንስተዋል።

ከንፁህ መጠጥ ውሃ ጋር በተያያዘም በተለይም ሽፋንን ለማሳደግ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በርካታ ፕሮጀክቶች ማስመረቅ መቻሉን በመጠቆም፤ በተያዘው በጀት ዓመትም በቡኢ፣ በዳሎቻ፣ በሺንሺቾ እና በዳንቦያ ከተሞች እንዲሁም በሀላባ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የውሀ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑም ለአብነት አንስተዋል።

የመስኖ አውታሮችን ከመዘርጋት ጋር በተያያዘም በክልሉ በርካታ የመስኖ አውታሮችን የማስፋፋት እንዲሁም ክፍተት የነበረባቸው ነባር የመስኖ አውታሮችን ወደ ስራ የማስገባት ስራዎችን መሥራት መቻሉን በመግለፅ በዚህም ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት በበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በሌሎችም ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለማልማት በተሰራው ሰራ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ከትራንስፖርት አንፃርም ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አዳዲስ የስምሪት መስመሮችን ከመክፈት ጀምሮ በርካታ ስራዎችን መስራት በመቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን በመግለጫው አንስተዋል።

በተለይም መናኸሪያዎች አካባቢ ከአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት እንዲሁም ከታሪፍና ከልክ በላይ ከመጫን ጋር ተያይዞ በተሰራው ስራ አበረታች ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል።

አክለውም ከታሪፍ ጋር በተያያዘ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በሁሉም መዋቅሮች በሚገኙ መናኸሪያዎች ተግባራዊ ተደሮጓል ያሉት ሀላፊው፤ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል ሰፊ ስራ መሠራቱንም አመላክተዋል።

በመጨረሻም በክልሉ በተለይም በመሠረተ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ዶ/ር መሃመድ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን