የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋግጥ ለትዉልዱ የለማችና አረንጓዴ የሆነች ሀገርን ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋግጥ ለትዉልዱ የለማችና አረንጓዴ የሆነች ሀገርን ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

”የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ኦሞ ዞን የ2017 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ መድረክ በበና ፀማይ ወረዳ ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልዕኮ እንደገለፁት፤ በዞኑ የሚገኙ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለትዉልዱ የለማችና አረንጓዴ የሆነች ሀገረን ለማስረከብ እየተሠራ ነው፡፡

በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች አምና የተከሰተዉ የመሬት መንሸራተት ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ ከዚህ ችግር በመማር ተራራማ አካባቢዎችን በተቀናጀ ተፋሰሰ ሥራ ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላረገዉ አድሱ፤ በዞኑ ከ35 ሺ ሄክታር መሬት በላይ በተቀናጀ ተፋሰሰ ልማት ለማልማት እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀው፤ በ6 ወረዳዎችና በ1 ከተማ አስተዳደር የንቅናቄ ሥራው በ46 ከፊል አርሶ አደርና በ90 አርብቶ አደር በድምሩ በ136 ቀበሌያት የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።

ኃላፊዉ አያይዘዉ ”የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል ወደ ተግባር የተገባዉ የተፋሰስ ልማት ሥራ የጠረጴዛማ እርከን፣ የአፈር ካብ፣ ትሬንች፣ ግማሽ ጨረቃ፣ ክትሮች እና ሌሎችም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስትራክቸሮች ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል።

የበና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንሰ ጋርሾ፤ በወረዳ ደረጃ በተከናወኑ የተፋሰስ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣት መቻሉን ገልፀው፤ ዘንድሮ በሚካሄደዉ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ሥራ በቡድን በማቀናጀት የተራቆቱና መልማት የሚችሉ ቦታዎችን ለይተዉ ወደሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት በተሰሩ የተፋሰስ ሥራ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘታቸዉን የሚናገሩት በአፈርና ዉሃ ጥብቃ ሥራ ላይ የተሳተፉ የአካባቢዉ አርሶአደሮች ለዘላቂነቱ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ግዳጁ ጎሮጊ – ከጂንካ ጣቢያችን