ከጠጠር ሜዳ እስከ ፕሪሚየር ሊግ

ከጠጠር ሜዳ እስከ ፕሪሚየር ሊግ

በአውሮፓ እግር ኳስ ማማ ላይ ዛሬ የምናያቸው ታላላቅ አሰልጣኞች ሚኬል አርቴታ፣ አንዶኒ ኢራኦላ እና ዛቢ አሎንሶ ስለ ስኬታቸው ሲጠየቁ መልሳቸው ወደ አንድ ነጥብ ይወስደናል – ሳን ሴባስቲያን።

እነዚህ ሶስት የፕሪሚየር ሊግ የትላልቅ ክለቦች አሰልጣኞች፣ በአለም እግር ኳስ ክብር ከመጎናጸፋቸው ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በባስክ ሀገር “አንቲጉኦኮ” በተባለ የሰፈር ክለብ የጠጠር ሜዳ ላይ አብረው ይጫወቱ የነበሩ የልጅነት ጓደኛሞች ናቸው።

አንቲጉኦኮ የላቀ የቴክኖሎጂ አቅም ያለው አካዳሚ አልነበረም።

በተቃራኒው በኮንክሪት እና በጠጠር ሜዳዎች ላይ የሚጫወት፣ ሀብት የሌለው ነገር ግን የባስክ እግር ኳስን አቅም የሚፈታተን የሰፈር ክለብ ነበር።

የአርሰናሉ ሚኬል አርቴታ፣ የሊቨርፑሉ አንዶኒ ኢራኦላ እና የቼልሲው ሻቢ አሎንሶ በአንድ ወቅት አንቲጉኦኮ ኪሮል ኤልካርቴያ በተባለ ትንሽ የባስክ ክለብ ውስጥ አብረው ተጫውተዋል።

ይህ ክለብ ምንም እንኳን “የልሂቃን አካዳሚ” ባይሆንም በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ እግር ኳስን እየመሩ ያሉ ታላላቅ አእምሮዎችን በማፍራት የዓለምን ትኩረት ስቧል።

ክለቡ የአሁኑን የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞችን ብቻ ሳይሆን፤ እንደ አሪትዝ አዱሪዝ ያሉ የላሊጋ ኮከቦችን ጨምሮ ከ40 በላይ ለከፍተኛ ሊግ የበቁ ተጫዋቾችን ያፈራ ድንቅ የችሎታ ማዕከል ነው።

የክለቡ ስፖርት ዳይሬክተር ሮቤርቶ ሞንቲኤል ስለ ሶስቱ ኮከቦች ሲያስታውሱ “ሚኬል አርቴታ ከልጅነቱ ጀምሮ የተወለደ መሪ ነበር” በማለት ያወሳሉ።

ዛቢ አሎንሶን ደግሞ “ጸጥታኛ ቢሆንም፤ በሜዳ ላይ ግን ድንቅ የጨዋታ አቀጣጣይ ነበር” ይላሉ።

አንዶኒ ኢራኦላ በበኩሉ “እጅግ በጣም ዓይናፋር፣ ነገር ግን ልዩ ተሰጥኦ ያለው ተጫዋች ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

የአንቲጉኦኮ የክለብ አመራሮች እንደገለጹት፤ እነዚህ ሦስት ተጫዋቾች ገና በስምንት ዓመታቸው ነበር ሜዳውን የተጋሩት።

እነዚህ ሶስት ተጫዋቾች በባስክ ሀገር ውብ ተፈጥሮ እና እግር ኳስ በተዋደደበት አካባቢ አድገው ዛሬ በዓለም ትልቁ መድረክ ላይ እርስ በርስ ሲፋጠጡ ማየት ለሰፈራቸው ክለብ ትልቅ ኩራት ሆኗል።

አንቲጉኦኮ የተመሰረተው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1982 ነበር። ክለቡ በሳን ሴባስቲያን ጠባብ ሰፈር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የፋይናንስ አቅሙ ውስን ቢሆንም “ከፍተኛ የትጋት ባህል” በመፍጠሩ ከ40 በላይ ተጫዋቾችን ወደ ከፍተኛ የሊግ ደረጃ ማድረስ ችሏል።

እነዚህ ተጫዋቾች እንደ ሪያል ማድሪድ እና ሪያል ሶሲዳድ ያሉ ግዙፍ ክለቦችን በወጣት ደረጃ መርታት ችለው ነበር።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በአንድ ውቅት ለምን ብዙ የባስክ አሰልጣኞች በእንግሊዝ እንደሚገኙ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ”ወደ ሳን ሴባስቲያን ሂዱና ከዚያ በኋላ ትረዱታላችሁ”ሲል ተደምጧል።

አንቲጉኦኮ በአሁኑ ወቅት ወደ ከፊል-ፕሮፌሽናል ደረጃ ያደገ ሲሆን፤ የድሮውን ጠጠር ሜዳ ወደ ዘመናዊ አርቲፊሻል ሜዳ ቀይሮታል።

ምንም እንኳን ትላልቅ ክለቦች ተጫዋቾችን በለጋ እድሜያቸው መውሰዳቸው ለአንቲጉኦኮ ተግዳሮት ቢሆንም፤ ክለቡ አሁንም አዳዲስ ተሰጥኦዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል።

እንደ ሚኬል አርቴታ፣ ሻቢ አሎንሶ እና አንዶኒ ኢራኦላ ያሉ ስሞች በአንድ ትንሽ የሰፈር ክለብ ውስጥ መገናኘታቸው የአጋጣሚ ብቻ አይደለም።

ይህ የጥረት፣ የትምህርት እና የጠንካራ የባስክ ስፖርታዊ ባህል ውጤት ነው።

አንቲጉኦኮ ለዓለም እግር ኳስ የሰጠው ትምህርት ቀላል ነው “በትንሽ ሜዳ ላይ ትልቅ ህልም ማለም ይቻላል።”

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ