የሚተከሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መርሐ ግብሮች የአየር ሚዛንን ከማስጠበቅ ባሻገር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚተከሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መርሐ ግብሮች የአየር ሚዛንን ከማስጠበቅ ባሻገር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመረዳት ሁሉም አካል ለመርሐ ግብሩ ትኩረት እንዲሰጥ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ተስፋን እንትከል ” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ የ2018 ዓ.ም ዞናዊ የክረምት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ንቅናቄ መድረክ በዎባ ኣሪ ወረዳ ተካሂዷል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በዚህን ወቅት እንደገለፁት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰተውን የአየር መዛባት ችግርን ለማስቀረት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።
ችግኞቹ በሚፈለገው ልክ ፀድቀው የተፈለገው ዓላማ እንዲሳካ እንክብካቤውን ተካዩ ማህብረሰብ በሀላፊነት መወጣት እንዳለበትም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
እንደ ዞን በ2018 ዓ.ም ከ27 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀቱን የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ኤልያስ ቃሾ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት የተተከሉ አረንጓዴ አሻራ ችግኞች በየአካባቢው በርካታ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ሲሉም አቶ ኤልያስ ተናግረው፤ በ2018 ዓ.ም ይፋ የተደረገው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች በንቅናቄ እንዲካሄድ ይደረጋል ብለዋል ሀላፊው።
የተተከሉ ችግኞች ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ የመሬት መራቆትን በመጠበቅና ሁሉ አቀፍ ውጤት በማስመዝገብ ተኪ የሌለው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የዎባ ኣሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መምህሩ ጌታቸው፤ የአካባቢ መራቆትን በማስቀረት ለሁሉ አቀፍ ለውጥ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ቀላል አይደለም ብለዋል።
እንደ ወረዳ ከ48 ሺህ በላይ ችግኞችም እንደሚተከሉም አቶ መምህሩ ገልፀዋል።
በተከላው የተሳተፉ አካላትም አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ማካሄድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦን በመገንዘብ በስራው በነቂስ እንደሚሳተፉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዞናዊ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ጎን ለጎን የ2018 ዓ.ም ዞናዊ የወጣቶች ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል።
በክረምቱ በ19 በተለየዩ ዘርፎች የወጣቶች ክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኣሪ ዞን ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ጽ/ቤት ሀላፊ ወጣት ግዛቸው ተሐም ገልጸዋል።
ሁሉም ወጣት በየአካባቢው በሚሠሩ 19 ዘርፎች የላቀ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ወጣት ግዛቸው አሳስበዋል።
ከ1 መቶ 53 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 7 መቶ ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጋል ሲሉም ወጣት ጌታቸው አብራርተዋል።
የኣሪ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አፌዶ ወርቁ በክረምት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ዞን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ለህዝቡ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀዋል።
በኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ መሪነት የዞኑ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች የአቅመ ደካማ ቤት አፍርሶ ለመገንባት በሚያስችል መርሀ ግብር የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ
መስራት እየቻሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች ለመፍታት የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ቀላል አለመሆኑ ተገለጸ
በስልጤ ልማት ማህበር ለ3ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተሰበሰቡ የአካባቢው ተወላጆች በዞኑ በሚገኙ የላንፉሮ ወረዳና ጦራ ከተማ አስተዳደር ችግኞችን ተክለዋል ።