በህገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት ከህግ፣ ከደህንነት እና ከማህበራዊ አንፃር ከባድ ችግሮችን እንደሚያስከትል ተገለጸ

በህገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት ከህግ፣ ከደህንነት እና ከማህበራዊ አንፃር ከባድ ችግሮችን እንደሚያስከትል ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት ከህግ፣ ከደህንነት እና ከማህበራዊ አንፃር ከባድ ችግሮችን እንደሚያስከትል የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

በሌላ መልኩ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ከሀገር መውጣት የዉጭ ምንዛሪ በማስገኘት ኢኮኖሚን የሚደግፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ መሆኑም ተገልጿል።

የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ እንደገለፁት፤ በህገወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት በዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።

ሞት፣ የአካል ጉዳትና የአዕምሮ መታወክ በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ችግሮች መሆናቸውን የተናገሩት ዳኛ ጥላሁን፤ በተለይ እንደ ሀዲያ ዞን አሁንም ወንዶች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሴቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በህገወጥ መንገድ እንደሚሄዱ አስረድተዋል።

በመዳረሻ ሀገራት ደግሞ እስር፣ ከሀገር መባረር፣ ህጋዊ የሥራ መብት እና ጥበቃ አለማግኘት፣ የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ አለማግኘት መኖሩንም ተናግረዋል።

ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚ አንጻርም ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚጋለጡ ዜጎች ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ፣ ለቤተሰብ መለያየት እና የስነ-ልቦና ጫና እንደሚዳረጉ አስረድተዋል።

የፓስፖርት፣ የቪዛ ወይም ሌሎች የጉዞ ሰነዶች ሳይሟሉ ከሀገር መውጣት ወይም ለመውጣት መሞከር የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልም አክለዋል።

በዞኑ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ እስከ 15 ዓመት የእስራት ቅጣት ዉሳኔዎች የተላለፉ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ድርጊቱን በህግ ስርዓት ብቻ መከላከል የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ በመተባበር መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

በሌላ መልኩ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ከሀገር መውጣት የዉጭ ምንዛሪ በማስገኘት ኢኮኖሚን የሚደግፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ መሆኑም ተናግረዋል።

ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የሥራ ውል እና ሌሎች የመንግሥት መስፈርቶችን አሟልተው ወደ ዉጪ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለሌሎች ችግሮች እንዳይጋለጡ ያደርጋል ሲሉም ዳኛ ጥላሁን አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን