የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በማጠናከር የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በማጠናከር የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

በኣሪ ዞን ባካዳዉላ ኣሪ ወረዳ የ2017 ዓም ዞናዊ የተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል ።

በኣሪ ዞን የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ መርሐግብርን በንግግር ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ወይኒቱ መልካ እንደገለፁት በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፈር መንሸራተት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስ በተሰሩ  የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሻለ ለዉጥ ማምጣት ተችሏል ።

የአፈር እና ዉሃ ጥበቃ ሥራዎችን በማጠናከር የሚፈለገውን የእርሻ ምርት ማሳደግ  እንደሚቻልም ቢሮ ሀላፊዋ አስረድተዋል ።

በክልል ደረጃ ሰፊ ዕቅድ ተይዞ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን በኣሪ ዞን ከ23 ሺህ ሄክታር  በላይ መሬት በአንድ ወር ለማልማት ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል ፡፡

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኣታ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለዉጥን በመቋቋም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻል ዘንድ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በተደራጀ አግባብ ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል ።

በኣሪ ዞን በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት 105 ንዑስ ተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከ212 ሺህ በላይ አርሶአደሮች የሚሳተፉበት እንደሆነ የገለፁት ደግሞ የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ ናቸው ።

የአካባቢው አርሶአደሮችም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የመጣውን ተጨባጭ ለዉጥ ለማስቀጠል ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል ።

ዘጋቢ ፡ ዳኜ ጥላሁን- ከጂንካ ጣቢያችን