ከ23 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 25/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር ከ23 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የ2018 የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዞናዊ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀምሯል።

“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በኦይዳ ወረዳ በተካሄደበት ወቅት የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤሊያስ፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ላለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

መላዉ የዞኑ ነዋሪዎችም ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እስኪፀድቁ ድረስ በመንከባከብ ግዴታቸዉን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ በዞኑ በ2011 ዓ.ም ላይ የተራቆተን መሬት ለመሸፈን እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖን ለመከላከል በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ202 ሚሊየን በላይ ችግኝ የተተከለ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ከ81 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን ስለመሸፈኑ ያብራሩት ኃላፊው የደን ሽፋኑ ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 21 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

የተተከሉ ችግኞች የመልከአ ምድሩን ገጽታ መቀየር የቻሉ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ያላቸው አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ዘንድሮው እየተተገበረ በሚገኘው ስምንተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ23 ሚሊየን በላይ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራና ስምንት ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀምበር መርሃ ግብር እንደሚተከሉም ተናግረዋል።

የኦይዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታዘበ ጋትሶ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር የአከባቢያቸው አየር ጸባይ እየተስተካከለ መምጣቱንና የደረቁ ምንጮች መፍለቅ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያዬት

በአረንጓደ አሻራ በአከባቢያቸው ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገ በመሆኑ በቀጣይ በመትከልና በመንከባከብ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ: አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን