የገሱባ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እያሻሻለ እንደሚገኝ ተገልጋዮች ገለጹ

የገሱባ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እያሻሻለ እንደሚገኝ ተገልጋዮች ገለጹ

ህብረተሰቡ ከሆስፒታሉ የሚያረካ አገልግሎት እንዲያገኝ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን በወላይታ ዞን የገሱባ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አስታወቀ ።

ወ/ሮ እታፈራዉ  ከበደ እና አቶ ዘለቀ መንገሻ ከሆስፒታሉ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆኑ የገሱባ መጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።

ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ በኩል አልፎ አልፎ ህብረተሰቡን ሲያማርር የነበረው የመድኃኒት ችግር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ ህብረተሰቡ የታዘዘለትን መድኀኒት በአግባቡ እያገኘ እንደሚገኝ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሳሙኤል ሳማ ተናግረዋል።በሆስፒታሉ ተኝቶ ለሚታከሙ ታካሚዎችና ለወላድ እናቶች ልዩ ክትትልና እንክብካቤ ከበፊቱ በተሻለ መልኩ እየተሰጠ እንዳለም ተመላክቷል።

እናቶችና ህፃናት በወሊድ ወቅት  አስፈላጊውን ክትትልና ሙያዊ አገልግሎት እያገኙ እንዳሉም  ከሆስፒታሉ ተገልጋዮች መካከል  ወ/ሮ የምስራች ደምሴ ገልፀዋል ።

የሆስፒታሉ ቀዳሚ ተግባር ህብረተሰቡ በበሽታ እንዳይጠቃ ቀድሞ  መከላከል መሆኑን የገለፁት የገሱባ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜድካል ዳይሬክተር ዶክተር ረድኤት አስፋው በበኩላቸው ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሻሻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።ተገልጋዩ  እሩቅ ሳይሄድ በአከባቢው የተሻለ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የቀዶ ጥገኛ ስፔሻልስት ዶክተሮች ተቀጥረው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ዶክተር ረድኤት ጠቁመዋል ።

የገሱባ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በአከባቢው የሚገኝ ብቸኛ ሆስፒታል ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን በሆስፒታል ደረጃ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳለ የገሱባ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት እርዳቸው ተናግረዋል ።

ዘጋቢ፡ሰላሙ ማሴቦ-ከዋካ ቅርንጫፍ