የተሻሉ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ

የተሻሉ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ ኢትሳ ገለጹ፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጀት ጂንካ ቅርንጫፍ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል።

ተቋሙ በስድስት ወራት አፈፃፀሙ ከመደበኛ ስራዎች በተጓዳኝ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና ከጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር የተለያዩ የድጋፍና የትብብር ስራዎችን ሲስራ መቆየቱ ተጠቁሟል።

ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ገረመው ሚደክሳ፣ ወንድማገኝ በቀለ፣ ወሰኑ ዶይዴና ሌሎች በሰጡት አስተያየት ተቋሙ በአብዛኛው ተግባራት የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡ የተሰማቸውን እርካታ ገልፀው፤ ለተግባሩ ስኬት አስተዋጽኦ ያበረከቱ አመራሮችን አመስግነዋል።

በተለይ በተቋሙ ቁልፍ ተግባር በሆነው በይዘት ስራዎች እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ዉጤቶችን በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ለመፈፀም ከታቀደው ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ብልሽት ጥገና፣ የንብረት አጠቃቀም፣ አቅዶ ከመስራት እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አፈፃፀም ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች በቀጣይ ወራት በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።

ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል።

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ ኢትሳ፤ የሚዲያውን ተደማጭነትና የማህበረሰቡን የመረጃ ተደራሽነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ ጋዜጠኞችና የዘርፉ ስራ መሪዎች በቁርጠኝነትና በኃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በበጀት አመቱ የተስተዋሉ አንዳንድ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከአጋር ድርጅቶችና አቻ የመንግስት ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሁሴን ዓለሙ – ከጂንካ ጣቢያችን