ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱ የትምህርት ጥራት በማስጠበቁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱ የትምህርት ጥራት በማስጠበቁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በጉራጌ ዞን በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ትኩረት ተደርጎ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የመማር ማስተማር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ማቲዎስ ማልደዮ፤ ቀደም ባሉ ጊዜያት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በተለይም ህጻናት በየደረጃቸው በተገቢው አውቀው ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዘዋወሩ በማድረጉ ላይ ውስንነት እንደነበርና ይህም በአጠቃላይ የተማሪው ውጤት ተጽእኖ ፈጥሯል ብለዋል።

ይህን መነሻ በማድረግም ክልሉ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በተገቢው እውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል በተለይም ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረው ይህም የትምህርት ጥራት በማስጠበቁ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

በክልሉ ከ5 ሺህ የሚልቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና መከታተላቸውንም አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ከአዲሱ ስርአተ ትምህርት ጋር ተያያዥነት ያለው እና በማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለአመቻቾችና ለመምህራን መሰጠቱ ህጻናት በሚመጥናቸውና በሚገባቸው መልኩ ከማስተማር ባሻገር በዘርፉ መምህራን ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች ይቀርፋል ብለዋል።

በዞኑ 10 የስልጠና ማእከላትን በማደራጀት ከመንግስትና ከግል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 1ሺህ 370 የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን ስልጠናው እንዲከታተሉ ተደርጓል ያሉት አቶ መብራቴ፤ በዋናነትም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለውጤታማነት መሰረት በመሆኑ የዞኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በዞኑ በመንግስትና በግል ትምህርት የሚሰጥባቸው 9 መቶ 34 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ከ3 መቶ 70 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መንደር ላይ ይገኛሉ ያሉት ሃላፊው፤ መምህራኑም መሰረታዊ ድጋፍ የሚሹ በመሆናቸው መሰል ስልጠናዎች አስፈላጊ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በተለይም ለአጠቃላይ የትምህርት ጥራት መጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱትን የቅደመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ለማጠናከር ዞኑ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ስለመሆኑ አስታውሰው፤ በዘርፉ የተፈለገው ውጤት እንዲመጣም ሁሉም ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ባለሙያ አቶ ባቂ በሰማ፤ ስልጠናው መምህራን ከስርአተ ትምህርቱ ጋር ተዋውቀው በተገቢው እንዲያስተምሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ህጻናት በደረጃቸው የሚገባቸውን እውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል በተግባር የተደገፈ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን