በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 38 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ስራ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 38 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ስራ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ በኋላ ብቻ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ነዋይ በክልሉ አፍሰዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል የቢሮ ሀላፊ እና የኢንቨስትመንት እና ዲያስፖራ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ኦሞ ሹሊ እንደገለፁት፤ ክልሉ ለኢንቨስትመንት አመቺ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመራጭ መዳረሻ እየሆነ ነው።

ግብርና፣ የማምረቻው እና የአገልግሎት ዘርፎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል የቢሮ ሀላፊው፤ ክልሉ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ ሳቢ አድርጎታል ነው ያሉት።

በአሁን ወቅት ከ1 ሺህ 5 መቶ በላይ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ ያሉ ሲሆን ከክልሉ ምስረታ በኋላ 300 ፕሮጀክቶች ዘርፉን በአዲስ መልክ ተቀላቅለዋል።

ለ125 ሺህ ዜጎች ደግሞ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ለዕውቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አቶ ኦሞ አብራርተዋል።

በክልሉ እየለሙ ያሉ የግብርና ኢንቨስትመንቶች የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት ባለፈ ተኪ ምርቶችን እያቀረቡ መሆኑም ተመላክቷል።

የክልሉ መንግሥት ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር እየሰራ ነው ያሉት አቶ ኦሞ፤ የመንገድና ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን በሟሟላት እና ሳቢ ፖሊሲ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ስራ ካልገቡ አልሚዎች ጋር በመነጋገር የገጠሟቸው ችግሮች ተቀርፈው ወደ ስራ እንዲገቡ ይሰራልም ብለዋል አቶ ኦሞ።

ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ