የሙያ ባለቤት በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተቋሙ የሚሠጡ ሥልጠናዎችን ትኩረት ሰጥተው እየተከታተሉ መሆናቸውን የዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሠልጣኞች ተናገሩ
በሙያ የተካኑ ምሩቃን ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ኮሌጁ አስታውቋል።
ተማሪ ኤልያስ አለመ እና እድላዊት ዘሪሁን በኮሌጁ የአግሮ ፉድ ፕሮሰሲንግ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሠልጣኞች ሲሆኑ፤ በተቋሙ ጥሩ የመማር ማስተማር ሂደት መኖሩንና በቀጣይ በሠለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ሥራ ለመፍጠር ማቀዳቸውን በመጠቆም ሌሎችም ይህንን ዕድል ያላገኙ ወጣቶች ወደ ተቋሙ መጥተው የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ተማሪ ኢያሱ ለገሰ እና ፍጹማዊት ጌታቸው በኮሌጁ የፋሽን ዲዛይን ዲፓርትመንት የመጀመሪያ ዓመት ሰልጣኞች ናቸው፡፡ እነሱም በሠለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የራሳቸውን የግል ኢንዱስትሪ እና የንግድ ተቋም በመክፈት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደው በመሰልጠን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
መምህር ፍቃዱ በየነ እና ጥላሁን በራሶ በኮሌጁ የአግሮ ፉድ ፕሮሰሲንግ እና የአውቶሞቲቭ ዲፓርትመንት አሰልጣኞች ሲሆኑ በኮሌጁ የተወሰነ የግብዓት እጥረት ቢኖርም ያለውን በአግባቡ በመጠቀም ለሠልጣኞቻቸው የክህሎት እና የተግባር ተኮር ሥልጠና እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥለጠና ዘርፍ አስተባባሪ እና የኮሌጁ ምክትል ዲን አቶ ሲሳይ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ በመደበኛ፣ በማታ፣ ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም በአጫጭር ጊዜ መርሐ-ግብር ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሠለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ኮሌጁ በሙያ የተካኑ ምሩቃን ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን አቶ ሲሳይ ተስፋዬ አስታውቀዋል።
ኮሌጁ 617 አዳዲስ እና 682 ነባር በመደበኛ መርሐ-ግብር የሚማሩ በድምሩ 1 ሺህ 299 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሠልጠን ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ