በንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እጦት እየተቸገሩ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የጅማ ወለኔ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

በንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እጦት እየተቸገሩ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የጅማ ወለኔ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

የጉራጌ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ማህበረሰቡ ላነሳቸው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

አቶ ኸይሩ አሊ፣ አብድልካፍ አስፋ እና ወ/ሮ ጎሀራም አበራ፤ በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የጅማ ወለኔ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ የከተማው ማህበረሰብ በንፁህ መጠጥ ውሀ እጦት እየተቸገረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀያ ሊትር ጀሪካን ለመሙላት እስከ አርባ ደቂቃ ይወስዳል ያሉት ነዋሪዎቹ ለዚህም ከለሊቱ 10:00 ጀምሮ ሰልፍ እንደሚይዙ አንስተዋል።

ለከተማው ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሀ ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ ተቆፍሮ ነበር ያሉት የጅማ ወለኔ ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ተማም፤ የጀነሬተሩ የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ ማስጠቀም አልቻልንም ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ማህበረሰቡን በማወያየትና ከወረዳው መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ትራንስፎርመር ገዝተናል ያሉት አቶ ሱልጣን፤ በተጨማሪም ለመስመር ዝርጋታና ለፕላን ለሀዋሪያት የደንበኞች አገልግሎት ክፍያ ብንፈፅምም ተቋሙ ችግሩን ሊፈታልን አልቻም ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሆሳዕና ዲስትሪክት የሀዋርያት የደንበኞች አገልግሎት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ባቢሶ በስልክ በሰጡን ሀሳብ፤ ለውሀ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አንስተው አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች ክልሉ ግብአቶችን በጊዜ ባለማቅረቡ ምክንያት የተፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ በበኩላቸው ማህበረሰቡ የሚያነሳቸው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት ከሆሳዕና ዲስትሪክት እየተነጋገሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

አቶ ዳርጌ አክለውም የውሀ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን