የጉራጌ ብሔር የልጃገረዶችን በዓል ነቖ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ

የጉራጌ ብሔር የልጃገረዶችን በዓል ነቖ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ

እንደ ዞን የበዓሉ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በእዣ ወረዳ የጉየና የስዋ ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከናውኗል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት፤ መምሪው ከዞኑ አስተዳደርና በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጉራጌ ማህበረሰብ የልጃገረዶች በዓል ነቖ ከማልማትና ከማስተዋወቅ ባሻገር የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየሰራ ነው።

የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ለሴቶች ይሰጠው ለነበረው ክብርና ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ነቖ አና አንትሮሸት የመሳሰሉ ሁነቶች ማሳያዎች ናቸው ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ መሰል እሴቶች በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ መምሪያው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የነቖ በዓል ለማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ሴት ልጃገረዶች ተሰባስበው ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት የደስታ በዓል ነው ብለዋል።

ለበዓሉ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግ የጠቆሙት ኃላፊዋ ለዚህም ሴት ልጃገረዶች ቤት ለቤት እየዞሩ ከቤተሰብ እስከ አካባቢ ነዎሪዎች ገንዘብን ጨምሮ በአይነት የገብስ፣ የአተር እና ሌሎች ስጦታዎች በመቀበል በበአሉ መጨረሻ እየበሉ፣ እየጠጡና እየጨፈሩ የሚደሰቱበት በዓል እንደሆነ ጠቁመዋል የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ።

ይህ ባህላዊ የልጃገረዶች በዓል ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመላክተዋል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የልጃገረዶች በዓል ነቖ እስከ ጥር ወር መጨረሻ በድምቀት እየተከበረ እንደሚዘልቅም ወ/ሮ መሰረት ጠቁመዋል ።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው፤ በዓሉ ባህላዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ለማድረግ የወረዳው አስተዳደር በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ባህል የአንድን ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚገለጽበት መሳሪያ ነው ያሉት አቶ ዘውዱ፤ የማህበረሰቡ ባህሎችን በተገቢው በመጠቀም በመንከባከብና በማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሺነሽ ተካ እንዳሉት በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ነቖ ሴት ልጃገረዶች ነጻነታቸውን የሚያውጁበት፣ ደስታቸውን የሚገልጹበትና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያጠናክሩበት በዓል ነው።

የጉራጌ ማህበረሰብ ነቖን ጨምሮ የበርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኑ ያነሱት ኃላፊዋ እነዚህን ማህበራዊ መስተጋብሮች ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

መሰል እሴቶችን በመታደግ እንዲለሙና እንዲተዋወቁ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በበዓሉ የተሳታፉ ሴት ልጃገረዶች እና እናቶች በዓሉ /ነቖ/ ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ወጥቶ በድምቀት መከበሩ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በዓሉ እንዲያንሰራራ መንግስት ለሚያደረገውን ጥረት አመስግነው በቀጣይ እሴቱ እንዲለማና እንዲተዋወቅ በማድረግ እንዲሁም የማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያጎለብት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን