በሁሉም ዘርፍ ለሚከናወኑ ስራዎች የመንገድ መሰረት ልማት ጠቀሜታው ፈርጀ ብዙ መሆኑ ተገለፀ

በሁሉም ዘርፍ ለሚከናወኑ ስራዎች የመንገድ መሰረት ልማት ጠቀሜታው ፈርጀ ብዙ መሆኑ ተገለፀ

በ2016 በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ የ3 ሺህ 11 ሰዎች ህይወት መቅጠፉንና በንብረት ላይ 4 ቢልዮን ብር ኪሳራ ማድረሱ ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ እያካሄደ ነው።

በንቅናቄ መድረኩ የጌዴኦ የዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ የሰው ልጅ በሚያደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የመንገድ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።

በዞኑ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች መሰራታቸውን ገልጸው፤ ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በሚያደርገው ጥረት ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዘብዴዎስ ኤካ(ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ትራንስፖርት የልማት ደም ስር ነው ብለዋል።

በክልሉ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና በሁሉም ሴክተሮች የሚከናወኑ ስራዎችን ለማሳለጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ቁልፍ መሆኑን ኃላፊው ተናግረው፤ ህብረተሰቡ በመንገድ ልማት ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መንግስት ከሚሰራቸዉ መሰረተ ልማቶች ባሻገር የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎም ያስፈልጋል ብለዋል።

የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ እና ንብረት በማውደም ብዙ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው የትራፊክ አደጋን ለመቀንስ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው።

የአደጋው አሳሳቢነት በክልሉ ከፍተኛ በመሆኑ ዛሬም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፌደራል መንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መሀመድ ሀሰን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ አነስትኛ የተሽከርካሪ ቁጥር ያላት ቢሆንም የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ነው።

በ2016 ዓ.ም የ3 ሺህ 11 ህይወት መቅጠፉና 4 ቢልዮን ብር በንብረት ላይ ኪሳራ ማድረሱንም ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አየለ ተካ