በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችና የበጀት አመዳደብ ሥርዓቶች የህፃናት መሠረታዊ መብትና ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ

በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችና የበጀት አመዳደብ ሥርዓቶች የህፃናት መሠረታዊ መብትና ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በህፃናት ፋይናንስ ዙሪያ ያጠናውን ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ የማድረግና የግንዛቤ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቀደሥላሴ ቤዛ፤ በዩኒሴፍ ድጋፍ በተለይ ከህፃናት መብትና ጥቅም ጋር በተያያዙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በስነ ህዝብ ልማት ተግባራት ውስጥ ታቅደው እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከዚህም ተግባራት አንዱ የፐብሊክ ፋይናንስ ለህፃናት ሲከናወን የቆየው የጥናት ሥራ አንዱ ነው ብለዋል።

የተሰጠው የግንዛቤ ሥልጠና ቀጣይ ውሳኔ ሰጪ አካላት ህፃናትን ማዕከል ያደረገ የፋይናንስ አመዳደብ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አዳማ ትንጳዬ፤ ህፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ጥናቱ እንደሚያመላክተው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ መዋቅሮች የህፃናትን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሴክተሮች ላይ የሚመደበው በጀት አናሳ ነው።

የውሃ ተቋማት አለመኖር ቀጥታ ህፃናት ለጤና ችግር እንዲጋለጡና ከትምህርት እንዲስተጓጎሉ የሚያደርግና በሀገሪቱ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ በጥናቱ ትኩረት እንደተደረገበት የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የማክሮ ኢኮኖሚ ጥናትና ሥልጠና ባለሙያ አቶ ዘካሪያስ ዛሳ ናቸው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ህፃናት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህፃናት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ምህረት በላይ መሰል፤ ጥናቶች መደረጋቸው የህፃናት ችግሮች እንዲቀረፉ ትኩረት መሰጠቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በህፃናት ጉዳይ ላይ የሚመደበው በጀት በቂ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ጥናቱ አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ላይ በትኩረትና በቅንጅት እንደሚሰራ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን