እርስ በርሳችን ከመቃቃር ይልቅ አንድነታችንን በሚያጠናክሩ ሀሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቶች አሳሰቡ
በወረዳውና በከተማ አስተዳደሩ “ዳራሮ ለአንድነት፣ ለልማትና ለዕድገት” በሚል መሪ ቃል የቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም ተካሂዷል።
በሲምፖዚየሙ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ የባህል አባቶች፤ የዳራሮ በዓል የሠላም፣ የበረከት፣ የአንድነትና የመቻቻል ባህላዊ እሴቶቻችንን በማንጸባረቅ አጠናክረን መቀጠል አለብንን ብለዋል።
“ዳራሮ ለአንድነት፣ ለልማትና ለዕድገት” በሚል መሪ ቃል የቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም መካሄዱን የተናገሩት የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሁሴን ጉሚና አቶ ተክሉ አለማየሁ፤ በቅርቡ በተካሄደው “የፋጭኤ” ንስሀ ባህላዊ የመንፃት ስነ- ስርዓት እርስ በእርስ ይቅርታ በተደረገው መሠረት ሁሉም ከመቃቃር ይልቅ አንድነትን በሚያጠናክሩ ሀሳቦች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የስራ ባህልን በማዳበር በልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ኃላፊዎች አሳስበዋል።
የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በሲምፖዚየሙ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ወጣቱ ባህልንና ቋንቋ ሥርዓቱንና ይዘቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አክለውም ሁላችንም በተሠማራንበት የስራ መስክ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በኢንቨስትመንትና በስራ እድል ፈጠራ እየተመዘገቡ ያሉትን ውጤቶች ለማስቀጠል ከወትሮው በተለየ ተቀናጅቶ መስራት ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶር) እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ አንድነታችንን በማጠናከር የተጀመሩ ለውጦችን በማስፋትና በማጠናከር ለልማት ይበልጥ መስራት አለብን በማለት አሳስበዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም ባህሎቻችንንና እሴቶቻችንን በማጠናከር ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በየደረጃው ያለው ማህበረሰባችን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ወጣቱ ትውልድ ባህልና የቋንቋ እሴቶችን በማጎልበት ለሰላም፣ ለልማትና ለዕድገት በቀጣይ በትኩረት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፅጌ ደምሴ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገለጹ
ከኑሮ ውድነትና ከኢኮኖሚ ችግር ለመላቀቅ ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም መስራት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአንደኛዉ የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ በእርሻ ዘርፍ ግብርናዉን ለማዘመን በተደረገዉ ጥረት የሰብል ምርታማነት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ