የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገለጹ
የህዳሴ ግድቡን እንደጀመርነው እናጠናቅቀዋለን እንዲሁም በህብረት ችለናል በሚል መርህ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉዲሼ እንደገለጹት፤ የመድረኩ አላማ ላለፉት 13 አመታት በራስ አቅም የጀመርነው የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅና በራሳችን አቅም እንጨርሰው ለሚለው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ ነው።
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ቀደም ሲል እንደተለመደው በቦንድ ግዥና በቀጥታ ድጋፍ የህዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነቱን ማሳየት እንዳለበት አሳስበዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሀላፊ አንባው ጬፋ ባቀረቡት የንቅናቄ ሠነድ ላይ እንደገለጹት፤ በህብረት ችለናል በሚል መሪ ቃል የህዳሴው ዋንጫ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአንድ አመት ይቆያል።
በመሆኑም የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ሀብት የማሠባሰቡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የአሪ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ይርዳው አሽኔ በበኩላቸው፤ ያለንን የራስ ሀብትና የህዝቡን አቅም መሠረት አድርጎ የተጀመረው የህዳሴ ግድብ ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው በመሆኑ ይህን ለማጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀረበው ሠነድ ዙሪያም ለቀረቡ ጥያቄዎች በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉዲሼ እና በአሪ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ይርዳው አሽኔ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከተሳታፊ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች መካከል ዶ/ር ኮማንደር መሀመድ፣ ወ/ሮ ንብረት ፍቃዱ እና ሌሎችም እንደገለጹት፤ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ የህልውናቸው ጉዳይ በመሆኑ አስፈላጊውን የቦንድ ግዥና ቀጥታ ድጋፍ በማድረግ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ