በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአንደኛዉ የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ በእርሻ ዘርፍ ግብርናዉን ለማዘመን በተደረገዉ ጥረት የሰብል ምርታማነት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ
ሀዋሳ፣ ጥር 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከአንደኛዉ የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ በእርሻ ዘርፍ ግብርናዉን ለማዘመን በተደረገዉ ጥረት የሰብል ምርታማነት እያደገ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ከመጀመሪያዉ የፓርቲዉ ጉባኤ በኋላ በግብርናዉ ዘርፍ ያልታዩ ዕድሎች እንዲታዩ በማድረግና የዉሃ አማራጮችን በመጠቀም በክልሉ የእርሻ ስራ ዉጤት ማምጣቱን የገለፁት የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ በክልሉ በዓመት የበጋ መስኖ ሽፋንን ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረዉን ሁለት ወይም ሶስት የምርት ወቅት አሁን ላይ የበልግ፣ መኸር፣ ፀደይ፣ የበጋ መስኖ እና አዲሱን የቅድመ በልግ አምስት የምርት ወቅት ማድረግ ተችሏል ያሉት ኃላፊዉ፤ ግብርናዉ የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር መፍቻ እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
የምግብና ስነ ምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ማረጋገጥ፣ ከዉጭ የሚገባዉን ምርት በሀገር ዉስጥ መተካትና ወደ ዉጭ የሚላኩ ምርቶችን ማምረት እንዲሁም ግብርናዉ የስራ ዕድል ምንጭ እንዲሆን ማድረግን ጨምሮ በተቀረፁ ስድስት ምሶሶዎች ተስፋ ሰጪ ዉጤት እየታየበት መሆኑንም ገልፀዋል።
ክልሉ “የተቀናጀ ግብርና ለቤተሰብ ብልጽግና” በሚል ሀሳብ የጀመረዉ ተግባር ስኬታማ እየሆነ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ኡስማን፥ በ30 40 30 የፍራፍሬ ልማትም ዉጤት መምጣቱን ተናግረዋል። በክልሉ ያልተለመዱ የፍራፍሬ ምርቶች በስፋት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተሰራበትና ዉጤትም እየተገኘበት ነዉ ብለዋል።
በባህር ዛፍ ተይዞ የነበረን መሬት ወደ እርሻ በመቀየር፣ በህገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረን የወል ቦታ ወደ ምርት በማስገባት እና ሌሎችን አማራጮች በመዉሰድ የማሳ ሽፋንን ለማስፋትና ምርታማነት እንዲጨምር መደረጉን ገልፀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሁሉም የምርት ወቅት ከ9 መቶ ሺህ ሄክታር በታች የነበረዉን የማሳ ሽፋን ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ማድረስ መቻሉን ገለፀዉ፤ የክልሉ ማዕከላዊ የሀገሪቱ አካባቢ መገኘትና ለማዕከላዊ ገበያ በቅርበት ላይ መሆን ለሚመረቱ ምርቶች መልካም ዕድል እንደሆነ አስታዉቀዋል።
ግብርናዉን ለማዘመን መንግስት የግብርና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረጉም ዉጤት እየታየ ነዉ ያሉት አቶ ኡስማን፥ በተለይ በክልሉ ሰፋፊ የኩታ ገጠም እርሻዎች የአርሶ አሰሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማቀራረብ የተሻለ ምርት እንዲገኝ እያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል። በኩታ ገጠም የበቆሎ ምርታማነት በክልሉ በሄክታር ከ75 ክንታል በላይ ማድረስ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፡ ድልነሳው ታደሰ
More Stories
በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችና የበጀት አመዳደብ ሥርዓቶች የህፃናት መሠረታዊ መብትና ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ
እርስ በርሳችን ከመቃቃር ይልቅ አንድነታችንን በሚያጠናክሩ ሀሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቶች አሳሰቡ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገለጹ