የሀዲያ ብሔር ጠንካራ የስራ ባህል እና የአንድነት ማሳያ የሆነውን የ”ወገኖ” ስርዓት ዕሴት ጠብቆ ለማቆየት እና ይበልጥ ለማስተዋወቅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በሀዲያ ዞን የጎምቦራ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
በዞኑ ጎምቦራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ ከብቶችን የማስመረቅ የ”ወገና” ስነ ስርዓት ተከናውኗል።
የሀዲያ ብሔር በርካታ ባህላዊ ዕሴቶችንና ክንዋኔዎችን ለዘመናት ጠብቆ ማቆየት ችሏል።
ከእነዚህ ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል ደግሞ የ”ወገና” ወይንም ከብት የማስቆጠር ስርዓት በጉልህ ይታወቃል።
ሀድዮች የጥረትን ውጤት በተዋበ ባህል የሚያስመርቁበት ስርዓት ‘መቶ’ ወይንም ‘ሺህ’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በብሔሩ አጠራር ደግሞ ‘ጢቢማ’ እና ኩሚማ ተብሎ ይጠራል።
በዚህ ስርዓት መሠረት ከብት ያስመረቁ ግለሰቦችም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የሚያገኙ ሲሆን ‘አበጋዝ’ ወይንም ‘ደዳቾ ‘የሚል ማዕረግ ይሰጣቸዋል።
በዞኑ ጎምቦራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ በተካሄደው ባህላዊ ከብት የማስመረቅ የ”ወገና” ስነ-ስርዓት ላይ አበጋዝ ኢዮብ ጎዴቦ፣ ደዳች ጡሚሲዶ አበሜ እና ደዳች ዶሌቦ ሾፎሬ ከዚህ ቀደም በ”ወገና” በባህላዊ ከብት በማስመረቅ ስርዓት ባህላዊ ማዕረግ ያገኙ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው ማህበር በየዓመቱ የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ አርብቶ አደሮችን በመለየት ይህንን ባህላዊ ስርዓት እንደሚያስፈጽሙ ገልጸዋል።
ከጥንት አባቶች ጀምሮ ሲተገበር የኖረው ይህ ዕሴት ከብት በሚያረቡበት ወቅት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍን የሚጠይቅ፣ ጠንክሮ የመስራት ውጤት፣ ጤናማ የዕድገት ፉክክር የሚያሰፍንና የባህላዊ አስተዳደር ስርዓት ማሳያ መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
በዕለቱ ባህላዊ ከብት የማስመረቅ ስነ-ስርዓት ቆጠራ የተደረገላቸው ደዳች ደገፈ ለቴ በበኩላቸው፤ ላለፉት ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን ተሻግረው ለዚህ ደረጃ መብቃታቸውን ገልፀው ህልማቸው እውን በመሆኑ ጥልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ለህልማቸው እውን መሆን የባለቤታቸው እና የወዳጆቻቸው እገዛ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ ከብቶችን በዙሪያው ላሉ አርቢዎች በማዋስና አቅም የሌላቸውን በማገዝ የተጣለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት እንደሚወጡ አስረድተዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ አንትሮፖሎጂስት እና በ”ወገና” ስርዓት ላይ ምርምር ያደረጉ አቶ ተፈራ ጋቦሬ በበኩላቸው የብሔሩ ድንቅ ባህላዊ ዕሴት የሆነው የ”ወገና” ስርዓት የባህላዊ ክዋኔዎች መንፀባረቂያ መድረክ መሆኑን በማንሳት ይህም የተለያዩ ስርዓቶችንና ሂደቶችን ተሻግሮ የሚፈጸም ክዋኔ ነው ብለዋል።
የአንድነትና የባህላዊ አስተዳደር ስርዓት የሚታይበት ይህ ዕሴት ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በወቅቱ የተገኙት የጎምቦራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ጎበና ጠንካራ የስራ ባህል ማሳያ የሆነው የ”ወገኖ” ስርዓት ሀዲያ ከሚታወቅባቸው ዕሴቶች አንዱ መሆኑን ጠቁመው ባህሉን ይበልጥ ማስተዋወቅ እና ለመጪው ትውልድ መሻገር ይገባል ብለዋል።
ይህን ባህል ሳይበረዝ ለመቆየት በሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም ተወላጆች የሀገር ሽማግሌዎች እና የመንግሥት አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የጉራጌ ብሔር የልጃገረዶችን በዓል ነቖ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ
በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችና የበጀት አመዳደብ ሥርዓቶች የህፃናት መሠረታዊ መብትና ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ
እርስ በርሳችን ከመቃቃር ይልቅ አንድነታችንን በሚያጠናክሩ ሀሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቶች አሳሰቡ