ፓርቲዉ ባለፉት 3 ዓመታት የብዝሃ ኢኮኖሚ መሪህ በመከተል እንደሀገር ዉጤታማ ተግባራትን ፈጽሟል-ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ  ቅድመ ጉባኤ የማጠቃለያ ክልላዊ ኮንፈረንስ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።

በኮንፈረንሱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ብልግጽና ሀገር በቀልና ሰዉ ተኮር ፓርቲ በመሆኑ ከትላንት የተሻለዉን በመዉሰድ ለነገ ጉዞ መሠረት የሚሆኑ መጠነ ሰፊ ለዉጦችን ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲዉ ባለፉት 3 ዓመታት የብዝሃ ኢኮኖሚ መሪህን በመከተል እንደሀገር ዉጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉንም አንስተዋል።

በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፉ ሀገር በቀል ስትራቴጂ በመከተል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም በመፍጠር ከፍተኛ ለዉጥ ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።በበጋ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኮርደር ልማት የታዩ ዉጤቶች ተጠቃሽ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዲፕሎማሲ ዘርፍም የሀገር ዳር ድንበርን ከማስጠበቅ ጀምሮ የብሔራዊ ጥቅምን ከማስቀጠል አንጻር ለዘመናት አይነኬ ተብለዉ በተለዩ መስኮችም ቢሆን በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ዉጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በክልሉ ለረጅም ጊዜያት ተጀምረው ባለመጠናቀቅ የህብረተሰቡ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በመመለሱ ረገድም የተሻለ ጥረት የተደረገበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል።

አሁን እንደሀገር እየታየ ያለዉን የኑሮ ዉድነት ችግር ለመቅረፍ የግብርና ስራዎች ላይ እየተሰጠ ባለዉ ትኩረት ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ዘርፉን ለማጠናከር በክልሉ ከ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የዶሮ ስርጭት መደረጉን ለአብነት ጠቁመዋል።

ክልሉ ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ ከነባሩ ክልል የተላለፈውን ዕዳ ለመቀነስ ወጪ ቆጣቢ የአመራር ስርዓት በመከተል ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የግብዓትና ሌሎች ዕዳዎችን መክፈል ተችሏል ብለዋል።

ባለፉት የለዉጥ ዓመታት በተለይም በትምህርት መስክ የሚታየዉን የጥራትና የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገው ርብርብ ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በማሰባሰብ ከ1 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።

ፓርቲው ሰዉ ተኮር እንደመሆኑ በዝቅተኛ ኑሮ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የአረጋውያን ቤት ግንባታን ጨምሮ የማዕድ ማጋራት ተግባራት በሰፊው እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ዝናብን ብቻ በመጠቀም ከዓመት አንዴ ብቻ የነበረውን አሰራር በመቀየር አነስተኛና መካከለኛ መስኖዎችን በማስፋፋት አሁን ላይ  ከ7 መቶ ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በድግግሞሽ እየታረሰ ነዉ ብለዋል።

በክልሉ የነበረውን የዉሃ ሽፋን ለማሳደግ በተደረገው ጥረትም ከ270 በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ4 መቶ ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዉ፥ በዚህም የክልሉን የንጹህ ዉሃ ተደራሽነት 2013 ላይ ከነበረበት 33 ነጥብ 7 በመቶ አሁን ላይ 43 በመቶ በላይ ማድረስ ተችላል ብለዋል።

በክልሉ ለተመዘገበው ዉጤት የአጠቃላይ ህዝቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በሁሉም ዘርፎች ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ባደረጉት ንግግር ፓርቲው በህዝብ ገፍነትና በድርጅት ሳቢነት ያልተለመዱ የሪፎርም መንገዶችን በመከተል ዉጤታማ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በተለይም ፓርቲው በተከተለው የመደመር መንገድ ከዚህ በፊት የነበሩ ስብራቶች በመጠገን ፍጥነትና ፈጠራን በተከተለ መልኩ የህዝብን የመልማት ፍላጎት ምላሽ እየመለሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ አንድ ትሩፋት መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቅሬ፤ ይህም የህዝቦችን የዘመናት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት ፓርቲው ያደረገውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያመለክት ነዉ ብለዋል።

ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ካስቀመጣቸዉ አቅጣጫዎች ዋነኛውን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተው፥ የአሁኑ ጉባዔም ባለፉት 2 ዓመት ተኩል የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ የፓርቲ ጉባኤ ለመሳተፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የተወጣጡ የፓርቲው አባላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ ፡ በአሰግድ ሣህሌ-ከቦንጋ ጣቢያችን