በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ኮካ ቀበሌ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የእንስሳት ክትባት እየተሰጠ ነው

“ወቅታዊ የእንስሳት ክትባት ለአርብቶ አደር ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ እንስሳትና ዓሣ ሐብት ልማት ዘርፍ ከክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ኮካ ቀበሌ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የእንስሳት ክትባት መስጠት ጀምሯል።

የእንስሳት ክትባት መደረጉ በቀንድ ከብቶቻቸው ላይ ይደረስ የነበረውን ጉዳት እንደሚቀንስላቸው አርብቶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች መካከል ከካፋ ዞን የጎባ ወረዳ፣ ከምዕራብ ኦሞ ዞን መኤኒት ጎልድያ፣ መኤኒት ሻሻ፣ ሱሪ፣ ማጂና ቤሮ ወረዳዎች አርብቶ አደሮች በብዛትና በስፋት የሚኖሩበት አካባቢዎች ናቸው።

ለአርብቶ አደሮች ደግሞ እንስሳት የኑሮ ዘዬአቸውና መተዳደሪያቸው መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በመሆኑም “ወቅታዊ የእንስሳት ክትባት ለአርብቶ አደር ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የክልሉ ግብርና ቢሮ እንስሳትና ዓሣ ሐብት ልማት ዘርፍ ከክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ኮካ ቀበሌ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የእንስሳት ክትባት መሰጠት ጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ምክትልና የኤክስቴንሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ በራሪ ሲራሉጉ እንደገለጹት፤ ክልሉ ለአርብቶ አደሩ የኑሮ መሠረት የሆነው እንስሳት ጤንነታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ክትባት በመስጠት ከወቅታዊ በሽታዎች ለመታደግ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የክትባቱ ዘመቻ የተጀመረ መሆኑን ያበሰሩት ሃላፊው፤ አርብቶ አደሮቹም ይህንን ዕድል በመጠቀም እንስሳትን በአግባቡ እንዲንከባከቡ አሳስበዋል፡፡

የክትባት ዘመቻው በእንስሳት ጤና ላይ የሚከሰተውን ወቅታዊ የጉርብርብ በሽታ ለመከላከል የሚረዳ በመሆኑ በተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ መጠቀም እንዳለባቸው የገለጹት በክልሉ ግብርና ቢሮ እንስሳትና ዓሳ ሐብት ልማት ዘርፍ የእንስሳት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ አለማየሁ ናቸው፡፡

የክትባቱ ዘመቻ ለአንድ ሳምንት የሚቀጥል በመሆኑ አርብቶ አደሩ፣ ባለሙያውና በየደረጃው ያሉት አካላት መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ ዶ/ር ብርሃኑ አሳስበዋል፡፡

በእንስሳት ጤና ላይ በየወቅቱ የሚከሰተው በሽታ በአርብቶ አደሩ ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ሕይወቱ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ሰፊ በመሆኑ ክልሉም ሆነ ዞኑ ለመከላከል መጠነ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሱሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባርዱላ ኦሊብሲኔ እና የምዕራብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዶማ ተናግረዋል፡፡

ወረዳውም ሆነ ዞኑ የተጀመረው መርሃ ግብር የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ክብቶቻቸውን ሲያስከትቡ ያገኘናቸው አርብቶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በእንስሳቶቻቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እንዲቻል እየተደረገ ያለው ጥረት እንዳስደሰታቸው ገልጸው ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በክትባቱ ዘመቻ መርሃ ግብር ላይ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ አመራር አካላትና ባለሙያዎች እንዲሁም የማህበረሰብ እንስሳት ጤና ሠራተኞች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን