ታራሚዎችን ከማረምና ማነጽ ባለፈ በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን የዕውቀትና የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ታራሚዎችን ከማረምና ማነጽ ባለፈ በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን የዕውቀትና የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጎፋ ዞን ቡልቂ ከተማ አካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ከሚሽን ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በክልሉ በሚገኙ ስምንቱ ማረሚያ ተቋማት ከ10 ሺህ በላይ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲታረሙና እንዲታነጹ በተቋማዊ ስትራቴጅክ ዕቅድ መሰረት አጽንኦት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከማረምና ማነጽ ባለፈ በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን የዕውቀትና የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ፍርደኞችና መደበኛ ቀጠሮ የሚከታተሉ ዜጎች በማረሚያ ቆይታቸው አስተሳሰባቸውና የስራ ባህላቸው ተቀይሮ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የኮሚሽኑን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት በኮሚሽኑ የበጀትና ዕቅድ ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ተመስገን ያዕቆብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ተቋማዊ የኮሚሽኑ የስድስት ወራት የተግባር አፈጻጸም፣ የመስክ ምልከታ ግብረ መልስና የኮሚሽኑና የማረሚያ ተቋማት መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ መወያያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ካነጋገርናቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኮማንደር ደጀኔ መርጫ፣ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ነረረ እና ኢንስፔክተር ብርቱካን መንግስቱ በሰጡት አስተያየት ጠንካራ ጎኖችን አጠናክረን በመቀጠል የሚታዩ ክፍተቶች ላይ በርትተን በመስራት ለተቋሙ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞን ጨምሮ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ በክልሉ ከሚገኙ ስምንቱ ማረሚያ ተቋማት የተውጣጡ የማኔጅመንት አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/