የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርባምንጭ ክላስተር ቢሮዎች የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀማቸውን ገመገሙ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርባምንጭ ክላስተር ቢሮዎች የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀማቸውን ገመገሙ

የግምገማ መድረኩ የተሻሉ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም ደካማ ጎኖችን ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርኘራይ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናግረዋል።

እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባምንጭ ክላስተር ከሚገኙ የሴክተር መስሪያ ቤቶች መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርኘራይዝ ልማት፣ ከተማና መሠረተ ልማት፣ ገቢዎች፣ ቴክኒክና ሙያ፣ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች ይገኛሉ።

እነዚሁ ተቋማት የሚያከናውኑት ተግባር የተሳካ እንዲሆን የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀማቸው የተገመገመ ሲሆኑ ተቋማቱ በክንውን ጊዜ የታየውን ጠንካራ ጎኖችንና እንደ ድክመት የታዩትን በመድረኩ አንስተዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቱሞ እንደገለጹት፤ የንግዱ ሥርዓት በህጉ መሰረት እንዲከናወን ከማድረግ አኳያ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

ህገ-ወጥ የቤንዚን ንግድን ከመቆጣር አንፃር ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ቢሆንም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ከኮሪደር ልማት ሥራ ጋር በተያያዘ ሁሉም ከተሞች በአቅማቸው ልክ ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው ከከተሞች ዕድገት ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሌሎች ክልሎችን ተሞክሮ አንስተው ተናግረዋል።

በመድረኩ ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ያለው አፈፃፀም በስፋት ታይቷል።

እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ስራዎች አንፃር በክልል ደረጃ ለስራ ዕድል ፈጠራ ተግባር የሚውልን በጀት ፈጥኖ ያለመላክ እንደ ተግዳሮት ተነስቷል።

ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘ ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉ ቢሆንም በታችኞቹ መዋቅሮች ወርዶ ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን የባለሙያ እጥረት እንደ ችግር ተነስቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርኘራይ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ እንደክልል 139 ሺህ 120 ህጋዊ ነጋዴዎች እንዳሉ ገልፀው 30 ሺህ የሚሆኑት ብቻ የንግድ ፈቃዳቸውን ማደሳቸው እንደክፍተት እንደሚነሳ ተናግረዋል።

ከነዳጅ ግብይት ጋር ተያይዞ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው ከእሁድ ገበያ ጋር በተያያዘም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሌማት ትሩፋት፣ ከህገ-ወጥ ግንባታ ጋር ተያይዞም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አቶ ገ/መስቀል ጫላ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን