የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ ዳራሮ በጨለለቅቱ ከተማ በደማቅ ሥነሥርዓት ተከበረ

ሀዋሳ፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ ዳራሮ በዓል በጨለለቅቱ ከተማ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው።

በዓሉ የምስጋና፣ የስጦታና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው።

ሥነ-ሥርዓቱ በአባገዳ መሪነት በ‘ሁሉቃ’፣ ‘ፋጎ’ እና ምርቃት የተከፈተ ሲሆን ለአከባቢውና ለሀገር ሠላምና አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና እንዲመጣ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲጠፉ ጸሎትና ልመና መደረጉን ተመላክቷል።

የጌዴኦ ሕዝብ የባህል መሪ አባገዳ ቢፎም ዋቆ ባስተላለፉት መልዕክት “ዳራሮ” የሰላም፣ የበረከት፣ የአንድነት፣ የልማትና መቻቻል እሴቶችን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ከሌሎች ወንድም ሕዝብ ጋርም ተስማምቶ መኖር ያስፈልጋል ብለዋል።

“ዳራሮ” ለአንድነት፣ ልማትና ዕድገት!” ብለን በጋራ እንዳከበርን እርስ በርስ ከመጠላላና ከመገፋፋት አባዜ በመውጣት አንድነታችንን በማጠንከር ወንድማዊነታችንን ለመጠበቅ፣ ለጋራ ልማትና እድገት በትኩረት መስራት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።

በዓሉን በንግግር የከፈቱት የጨለለቅቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ፈይሳ የምስጋና እና የስጦታ እንዲሁም የአዲስ አመት ማብሰሪያ “ዳራሮ በዓል” አባቶች ያቆዩት ብርቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን ገልፀው ሁሉም በአግባቡ በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሥራት እንደሚገባው አስረድተዋል።

የኮቾሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ጌታቸው በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የዳራሮ በዓል በሕብረተሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

አያይዘውም በዓሉ ለማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ የተጀመረውንም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በተግባር በመደገፍ ጭምር በዓሉን መክበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

አቶ ታጠቅ ዶሪ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ በበኩላቸው የዳራሮ በዓል የጌዴኦ ብሔር ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከባብሮና ተስማምቶ እንዲኖር መልካም ዕድሎችን የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርብ ጊዜያት በዞኑ በተከናወኑ “የፋጭኤ” ባህላዊ የንስሐ ሥነሥርዓት አማካኝነት በሁሉም የሥራ ዘርፎች የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አስረድተው ይህን በጎ ምግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ቀደምት አባቶች ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩልንን ባህላዊ እሴቶቻችንን ሁሉም በአግባቡ በመረዳት ይዘቱንና ውበቱን ሳይለቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን