ጽህፈት ቤቱ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ማመዴ ቀበሌ ላስገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽ/ቤት ሲኒየር የፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ መንበረ ገብረኤል የቁሳቁስ ድጋፉን ለአበሽጌ ወረዳ አስተዳደር ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ጽ/ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በመላው ሀገሪቱ 34 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቶ ለተማሪዎች ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎንም ጽ/ቤቱ ለመማር ማስተማር አገልግሎት የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደርጋል።
በጉራጌ ዞን በአበሽጌ ወረዳ ማመዴ ቀበሌ ለረገ ኤያት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም ለሴቶች የሚሰጣቸው የንጽህና መጠበቂያ ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ያደርጋል ብለዋል ዳይሬክተሯ።
በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሚሰጠው የማበረታቻ ሽልማት ሌሎች ተማሪዎች ተመሳሳይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እና እንደሀገር በመማር ማስተማሩ ሂደት ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ያሉት ወ/ሮ መንበረ፤ ጽህፈት ቤቱ በመላው ሀገሪቱ በሚያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች የሚያደርገው ድጋፍ ቀጣይነት ያለው እንደሆነም ጠቁመዋል።
የቁሳቁስ ድጋፉን የተረከቡት በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በወረዳው ለረገ ኤያት ትምህርት ቤት ላበረከቱት የቁሳቁስ ድጋፍ አመስግነው መሰል ድጋፎች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል።
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት አማካኝነት ለረገ ኤያት ትምህርት ቤት ከተደረገው የመማሪያና ሌሎች ድጋፎች በተጨማሪ ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ በመውጣት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ታብሌት መሸለማቸውን የተናገሩት አቶ ካሱ ሽልማቱ በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በወረዳው ለአምስት ቀበሌዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኘው ለማመዴ ጤና ጣቢያ የህክምና ግብዓት ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ማህበረሰቡ የለውጡ መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ ኑሮ ለማሻሻል የሚያከናውናቸው ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ ለመደገፍ እያደረገ ያለው ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በረገ ኤያት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከየክፍላቸው በትምህርታቸው የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የታብሌት ሽልማት የተበረከተላቸው ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በተሰጣቸው ሽልማት መደሰታቸውን ገልጸው፤ ሽልማቱ በቀጣይ ውጤታቸውን የበለጠ ለማሻሻልና ሌሎች ተማሪዎች የነሱን አርአያነት ያለው ተግባር ተከትለው በትምህርታቸው ጠንካራ በመሆን የተሻለ ውጤት አምጥተው ተሸላሚ ለመሆን መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/