ሀዋሳ፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሆሳዕና እና አከባቢ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሶሎ መዘምራን ሕብረት ከሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለተወጣጡ አቅመ ደካሞች ከ276 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያለውን ዱቄትና ዘይት ድጋፍ አደረጉ።
የበጎ አገልግሎት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም የሀዲያ ዞን አስተዳደር ገልጿል።
የሆሳዕና እና አካባቢው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሶሎ መዘምራን ሕብረት አስተባባሪ ዘማሪ ዮሴፍ ሳሙኤል ሕብረቱ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሸገር ከዚህ ቀደም በተለያዩ በጎ ተግባር አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ እየሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዕለቱ ከሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለተወጣጡ ለ100 አቅም ደካሞች ከ276 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄትና 3 ሊተር ዘይት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።
ወጪው ሙሉ በሙሉ ደቡብ አፍርካ ከሚገኘው ቪራይት ኤፍ ቢ አይ ቤተክርስቲያን የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል ።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማው የጽዳት ዘመቻ ስራን መስራታቸውን ገልጸዋል ።
የአሁኑ ድጋፍ ለሁለተኛ ዙር መሆኑን የተናገሩት ዘማሪ ዮሴፍ፥ በቀጣይም ይኸው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል ።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው መንግስት ከጀመረው ሰዉ ተኮር ተግባር አቅመ ደካሞችን መርዳት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።
ከንቲባው አክለውም ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበው ሁሌም ተረጂ ሆኖ መኖር ሳይሆን የተሰጠንን ዕድል በመጠቀም ሠርቶ ለመለወጥ መትጋት እንዳሚገባ አሳስበዋል ።
በድጋፍ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙ የሀዲያ ዞንዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ታምራት አኑሎ የተቸገሩትን መርዳት በሁሉም ዘንድ ዋጋ ያለው በጎ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል ።
ይህ በጎ ድጋፍ ሰብአዊና ሐይማኖታዊ ኃላፊነት በመሆኑ በሁሉም ዘንድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/