ሀዋሳ፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሕዝቡ ቦንድ በመግዛት ያካበተውን የቁጠባ ባህል በማጠናከር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሂደት ማሳካት እንደሚቻል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጂንካ ቅርንጫፍ አስታወቀ።
በኣሪ ዞን በየደረጃው የህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል።
ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ በገዙት ቦንድ ገንዘብ በመቆጠብ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻሉም ተጠቃሚዎች ተናግረዋል ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጂንካ ቅርንጫፍ ገሽ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ ኦርካይዶ ኩሴ እንደገለፁት የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ከማድረስ ባለፈ የሕዝብን አንድነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ሕዝባዊ ፕሮጀክት መሆኑን ማረጋገጥ የተቻለበት እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል።
ቀሪውን የግንባታ ሂደት ለማጠናቀቅም ሕዝቡ ያካበተውን የቁጠባ ባህል ቦንድ በመግዛት እንዲያጠናክር አቶ ኦርካይዶ ጥሪ አቅርበዋል።
ቀደም ሲል ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ የቦንድ ግዢ በመፈፀም የቁጠባ አቅማቸውን ማሳደግ የቻሉ አስተያየት ሰጪዎች ቦንድ መግዛት ” በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ …” እንድዲሉ በአንድ ጎን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሥራ በማገዝ፣ በሌላ በኩል ቁጠባን ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል ።
ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ