የቤንች ብሄር ያለውን ባህልና ቋንቋን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ

የቤንች ብሄር ያለውን ባህልና ቋንቋን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ጥር 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቤንች ብሄር ያለውን ባህልና ቋንቋን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናግረዋል፡፡

የቤንች ብሄር የዘመን መለወጫና የምስጋና  በዓል ”ቢስት ባር” በማክበር የቤንች ብሄር ባህልና ቋንቋ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል፡፡

 የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን እንደተናገሩት ለዘመናት ተቋርጦ የቆየው የዘመን መለወጫ በዓሉ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በድምቀት ለማክበር መቻሉን ተናግረዋል።

ከቤንች ብሄር ቱባ የባህል እሴቶችና ሀብቶች ውስጥ ዛሬ በፓናል ውድይት ያሰባሰበን የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓላችን የሆነው “ቢስት ባር” ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ነው ያሉት፡፡

በዓሉ የብሔሩን ባህልና እሴት በሚገባ ተጠብቆ በየጊዜው መከበር እንዲቻል በቅንጅት መሰራት አለበት ብለዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ እንደገለፁት የቤንች ሸኮ ዞን ህዝብ የሚያኮራ ታሪክና ባህል ያለን ህዝቦች ነን ብለዋል።

አዲሱ ትውልድ ባህላችንና ታሪካችንን ከኛ በተሻለ እንደሚያሳድገው በቢስት ባር ተመልክቻለሁ ያሉት ኃላፊው በዞኑ ህዝብና አመራር ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

በተለይ የቤንች ብሄር ያለውን ቱባ ባህልና እሴቶችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍና ቋንቋውንም ይበልጥ ለማሳደግ እንዲቻል ምሁራን ጥናትና ምርምሮችን አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የቋንቋና ስነ-ፅሁፍ መምህር የሆኑት ዕጩ ዶክተር ትዕዛዙ አቲሞ በብሔሩ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ የተዘጋጀውን ጥናታዊ ፅሁፋቸውን አቅርበዋል።

በፓናል ውይይቱ  ላይ የፌደራልና የክልል የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ምሁራን  እና ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ  ክፍሎች ተሳታፊዎች ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን