ባህላዊ ዕሴቶችን ለማስተዋወቅ የባህል ኪነት ቡድን ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወረዳው ያሉ ባህላዊ ዕሴቶችን ለማስተዋወቅ የባህል ኪነት ቡድን ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን የከና ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴት ለማስተዋወቅ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነ የወረዳው ባህል ኪነት ቡድን አባላት ገልጸዋል፡፡
በኮንሶ ዞን ከና ወረዳ ካነጋገርናቸው የባህል ኪነት ቡድን አባላት መካከል አቶ ደያሳ ተፈሪና ወ/ሮ ካታና ካሮ በተለያዩ መድረኮችና ዝግጅቶች የተለያዩ ትዕይንቶችን በማሳየት የህዝቡን ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው ብለዋል።
ወ/ሪት ካሰች ከሽለና እና አቶ ኩማቾ ኩዲሼ በሰጡት አስተያዬት የተለያዩ ዝግጅቶችን ለህዝብ በሚቀርቡበት ጊዜ የማህበረሰቡን ማንነት የሚገልጹ አለባበሶች፣ ጌጣጌጦች፣ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንዲሁም የፀጉር አሰራር ይዘው እንደሚቀርቡ ገልፀዋል።
የኪነት ቡድን ሥራ፣ ጊዜና ዝግጅት እንዲሁም ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ የሚናገሩት የቡድኑ አባላት፥ ከህዝብና ከመንግሥት ድጋፍ ያሻል ብለዋል።
የከና ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞሎ ሞዶልቴ ባህላዊ የኪነት ቡድን ባህላዊ ዕሴቶችና ማንነትን ለማስተዋወቅ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው ባህላዊ የኪነት ቡድን ከተቋቋመ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በዕድሜ መግፋትና ትኩረት ማጣት የተነሳ ተበትነዋል ያሉት ኃላፊ፥ በአዲስ መልክ የማቋቋምና የማጠናከር ሥራ እንደተሰራ ተናግረዋል።
በወረዳው በተለምዶ ኮንሶ ኒዮርክ የሚባል የተፈጥሮ ቅርስ፣ የፍል ውሃ፣ በኮንሶ ባቲካማ የሚባል ትልቁ ተራራ የሚገኝበት፣ ቱርካ ናማ የሚባል የመጨረሻ የጥፋት ውሳኔ የሚተላለፍበት ስፍራ እንደሚገኙም አውስተዋል።
ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ጥብቅ ደኖች፣ ውብ እርከኖች እንዲሁም ከኮንሶ ህዝብ አኗኗር ጋር ጥብቅ ትስስር ያላቸው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሉበት በመሆኑ፥ የባህል ቡድኑ አከባቢውን ከማስተዋወቅም ባሻገር የማልማት ሥራዎች በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ የአማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ፓርቲዉ ባለፉት 3 ዓመታት የብዝሃ ኢኮኖሚ መሪህ በመከተል እንደሀገር ዉጤታማ ተግባራትን ፈጽሟል-ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ኮካ ቀበሌ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የእንስሳት ክትባት እየተሰጠ ነው
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላማዊ መንገድ ተከብረው እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ