በእንስሳት እርባታና በጓሮ አትክልት ሥራ በመሰማራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ

በተያዘው በጀት ዓመት ከ40 ሺ በላይ አባወራ በከተማ ግብርና ተጠቃሚ ማድረጉን የአረካ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በከተማ አካባቢ ያለውን ውስን መሬት በመጠቀም እጅግ ፈታኝ የሆነውን የከብትና የዶሮ እርባታ እንዲሁም የጓሮ አትክልት በማምረት ተጠቃሚ ከሆኑት በአረካ ከተማ የመሀል ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ አበበ ቲቶና አቶ አቡዱሩማን ከድር፤ የወተትና የእንቁላል ምርት ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ለእንስሳት አስፈላጊ የሆኑ ህክምናና የምርጥ ዘር አቅርቦት ማግኘታቸውን ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸውም አስረድተዋል።

የሌማት ትሩፋትና የምግብን ከጓሮዬ ፕሮግራሞች እንደሀገር የተጀመረው እንቅስቃሴ መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው የገልፁት ነዋሪዎቹ፤ መንግስት ያመቻቸውን ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አልሸሸጉም፡፡

ስለ ሌማት ትሩፋት በቂ ግንዛቤ በመፈጠሩ ለውጥ መምጣቱን የሚናገሩት በከተማዋ ግብርና ጽ/ቤት የእርባታ ባለሙያ አቶ ግርማ ጊዴቦ፤ በከተማዋ የወተት ሀብት በእንቁላልና የስጋ ዶሮዎችን የሚያረቡ በግልና በማህበር ለሚሰሩ ድጋፍና ክትትል በመደረጉ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የአረከ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ አሳሌ በበኩላቸው፤ እንደሀገር የተጀመረው የከተማ ግብርና ልማት ሥራ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በከተማዋ ባሉት ዘጠኝ ቀበሌያት 17 የወተት መንደርና 16 የዶሮ መንደር እንዲሁም የማርና የስጋ መንደር እንዳሉም አብራርተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከ40 ሺ ላይ አባወራ በከተማ ግብርና በማህበርና በግል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያነሱት ኃላፊው፤ የከተማ ግብርና በማዘመን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን