ሀዋሳ፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ከጠልቃ ገብነት፣ ከዕንግልትና ገንዘብ ብክነት በፀዳ መልኩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኢምግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ አስታወቀ።
ቅርንጫፉ ከ2016 ታህሳስ ጀምሮ እስከሁን ከ130ሺ የሚበልጥ ፓስፖርት ለተገልጋይ መስጠቱን አስታውቋል።
የአንድ ሀገር ዜግነትን በአለም አቀፍ የሚገልጸው ፓስፖርት ሲሆን ፓስፖርት የሚሰጠው ተቋም ደግሞ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ነው።
በኢትዮጵያ ፓስፖርት እና ዜግነት አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አለሙ እንደገለጹት ቅርንጫፉ በዋናነት ለደቡብ ኢትዮጵያ፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በስራና በሌላ ምክንያትም ከተለያዩ አከባቢዎች መጥተው ነዋሪ ለሆኑ ዜጎችም አገልግሎት ይሰጣል።
ፓስፖርት ሳይዙ ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ መሞከር ወንጀልና ህገወጥ መሆኑን የገለጹት አቶ አማኑኤል ማንኛውም ዜጋ አስፈላጊ መስፈርቶችን አሟልቶ ከመጣ ፓስፖርት ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።
ቅርንጫፉ አዲስ፣ ዕድሳት፣ አስቸኳይ እና የጠፋውን ፓስፖርት የመስጠትና የስም ማስተካከያ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን እያንዳንዱ አገልግሎት ከህትመት ቁጥርና ከሚሰጠው ኮታ አንጻር የቀጠሮ ቀን ልዩነት እንደሚኖር አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ተገልጋዮች ከግንዛቤ እጥረት አስፈላጊ መስፈርቶችን ሳያሟሉ እና ሌሎች ተገልጋይ ያልሆኑ ሰዎችን ከጎናቸው ይዘው በሚመጡበት ወቅት በተቋሙ አሰራር ሂደት ላይ ማስተጓጎል ከመፍጠራቸውም ባሻገር ለገንዘብ ብክነት እና ለእንግልት ሊዳርጉ እንደሚችሉ አቶ አማኑኤል ጠቁመዋል።
ከ2016 ታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ከ130ሺ በላይ ፓስፖርት ለተገልጋይ መስጠት ተችሏል ያሉት አቶ አማኑኤል ከዚህ ውስጥ ከ70 ሺ በላይ በዘንድሮ የተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አገልግሎቶቹ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፓስፖርት ቁጥርን በማሳደግ የተለያዩ አገልግሎቶችን የያዘ ኤሌክትሮኒክስ አዲስ ፓስፖርት ከመስከረም ወር ጀምሮ ለመስጠት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ከአቶ አማኑኤል ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።
ማንኛውም ተገልጋይ ያልሆነውን ሰው ሳያስከትል በመምጣት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ካጋጠመ ቢሮ ገብቶ ባለድርሻ በማናገር ችግሮቹን መፍታት ይቻላል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዕለቱ አገልግሎት እያገኙ ከነበሩት አንዳንድ ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም አገልግሎት ለማግኘት ብዙ መመላለስ፣ ዕንግልትና የገንዘብ ወጪ እንደነበር ገልጸው አሁን ግን በዕለቱ ማግኘት የሚችሉትን አገልግሎት በዕለቱ ጨርሰዉ እየሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ወጣቱ በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ እንዲያመጣ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዞኑ በሚኖረው ቆይታ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ
ከ14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሠማራታቸው ተገለጸ