የግል ጤና ተቋማት ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው ተገቢ ግልጋሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የግል ጤና ተቋማት ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው ተገቢ ግልጋሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው የደቡብ ምእራብ ክልል የግል ጤና ተቋማት ማህበር አሳሰበ።
የቤንች ሸኮ ዞን የግል ጤና ተቋማት ማህበር የ2017 ጉባኤውን አካሂዷል።
የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ሽፋን 48 ከመቶ የሚሸፍነው የግል የጤና ተቋማት እንደሆነ ተመላክቷል።
የደቡብ ምእራብ ክልል እንደ አዲስ ከተመሰረተ በኋላ የግል ጤና ተቋማት ማህበርም ከቀድሞው የደቡብ ክልል ወጥቶ እራሱን ችሎ በስድስት ዞኖች 1ሺ 900 አባላት ይዞ በግል ጤና ተቋማት ማህበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ክልል የግል የጤና ተቋማት ማህበር ምክትል ሰብሳቢው አቶ ፍሬዘር ከተማ ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ የግል ጤና ተቋማት ማህበር በክልሉ ከሚገኙ ማህበራት ጠንካራ እና ሞዴል መሆኑን ጠቅሰው፥ ነገር ግን የመረጃ አያያዝ እና ሪፖርት በወቅቱ ያለማቅረብ ችግሮች በማህበሩ እንደሚታይ አስታውቀዋል።
ከቅንጅት አንጻርም ክፍተት መኖሩን ያነሱት አቶ ፍሬዘር፥ በተለይም በግል ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮች ሊፈቱ ይገባልም ብለዋል።
ለአብነት ያሉትንም ሲያነሱ የባለሙያ ስነምግባር የመድኃኒት ከዶዝ በታች መስጠት፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ጥራት ችግሮች መኖር፣ በወቅቱ ሪፈር አለማድረግ በአንዳንድ የግል የጤና ተቋማቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ሊታረሙ ይገባል ብለዋል።
ከባለሞያዎቹ መካከልም አቶ ሄኖክ ታፈሰ እና አቶ ደረጀ እንዲሁም አቶ በላይ ያ፣ ጋሻው ተመስገን እንደተናገሩትም ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ማህበሩ ተገቢ ክትትል በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለአብነት እንደ ችግር ያነሱትም የማይሰሩ ማይክሮስኮፖችን ማስቀመጥ ፣ ከደረጃ በታች ለህሙማን መድኃኒት መስጠት፣ በተገቢው የመድኃኒት ማዘዣ አለመጻፍ ፣ የባለሙያ ስነምግባር ችግር መኖር ጉድለት ነው ብለዋል።
ከአንዳንድ የመንግስት ህክምና ተቋማትም ቢሆን ታካሚውን ከዚህ መድኃኒት ቤት ግዙ ተብሎ ከማዘዣው ጀርባ የሚጻፈው ነገር ተግዳሮት ነውም ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ተወካይ እና የጤና እና ጤና ነክ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ዳይሪክቶሬት ዳይሪክተር አቶ ለገሰ ግርማይ በበኩላቸው ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው የሚሰሩ የግል ጤና ተቋማት እንዳሉ ሁሉ ጉድለት ያለባቸውን መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከመድኃኒት አቅርቦት አንጻር ከደረጃ በታች እና በዝቅተኛ ዋጋ ከተለያዩ ቦታዎች የሚቀረቡት መድኃኒቶችን ባለመግዛት የግል ጤና ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ከባለሙያ ስነምግባር አንጻርም ጋዋን በተገቢው አለመልበስ፣ ያልተሟሉ ግብአቶች እንደተሟሉ አድርጎ ማስታወቂያ መስራት፣ ከተፈቀደላቸው ፍቃድ በላይ አገልግሎት መስጠት፣ መድኃኒት ከዶዝ በታች መሸጥ ተግዳሮት በመሆናቸው ባለሙያዎች ይህንን ችግር ቀርፈው በተገቢው ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
ማህበሩም የጀመረውን ቅንጅት አጠናክሮ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን በተላለፈው ውሳኔ መደሰታቸውን የእዣ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
አሊያንስ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቀ
በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመጡ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዉ መቀጠል ይኖርባቸዋል – የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ