የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን በተላለፈው ውሳኔ መደሰታቸውን የእዣ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ምክር ቤት አባላት የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን በጉራጌ ዞን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ በወረዳቸው ተግባራዊ በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል።
ከእዣ ወረዳ ምክርቤት አባላት መካከል አቶ ደንድር ፍታ፣ አበበ አመርጋ፣ ፈቀደ ወልዴና ወይዘሮ ከድጃ ተማም በጉራጊኛ ቋንቋ የምክርቤት ምክክር በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልፀው አባላቱ ጥያቄ መጠየቅና የአስፈፃሚ አካላትን ምላሽና ማብራሪያ በጉራጊኛ እንዲሆን ተግባራዊ መደረጉን አድንቀዋል።
የጉራጌ ዞን ምክርቤት ጉራጊኛ ቋንቋ በዞኑ ወስጥ በሚገኙ መዋቅሮች ሁሉ የስራ ቋንቋ ማድረጉ ተገቢ ውሳኔ መሆኑን ያነሡት አባላቱ በአጭር ቀናት ውስጥ በወረዳቸው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ተግባር ቋንቋውን ከመሞት የሚታደግ በመሆኑ ጉራጌ ዳግም የተወለደበት ቀን እንደሆነ እናስበዋለን ያሉት አባላቱ፥ ቋንቋ ለአንድ ማህበረሰብ ሀሳብ ከመግለፅ ባሻገር ማንነት የሚያሳይ መሆኑና ቋንቋው የተረሳና የጠፋ ብሔር ቀስ በቀስ ማንነቱ የመጥፋት አደጋ ስለሚጋረጥበት በተቻለ መጠን ቋንቋው ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
የእዣ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ሙከረም በደዊ በወረዳው 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 47ኛ መደበኛ ጉባኤ በተደረገበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የጉራጌ ዞን ምክርቤት የጉራጊኛ ቋንቋ የሚዲያ የትምርትና የስራ ቋንቋ እንዲሆን ባፀደቀው መሠረት በወረዳው ተግባራዊ መሆኑን አመላክተዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ ጉራጊኛ ቋንቋን ለማሳደግ የተጀመረው ቋንቋውን የትምህርት፣ የሚዲያና የስራ ማድረግ ጅማሬ ለማሳደግ በዚህ ቋንቋ አፍ የፈታ ተወላጅ ሁሉ በመናገርና በመፃፍ ተግባራዊነቱ ሊያስቀጥል እንደሚገባ አውስተው ለምክርቤቶችም ሪፖርት በጉራጊኛ እየቀረበ የሚቀጥል በመሆኑ ከወዲሁ ዝግጅት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
ጉራጊኛ ቋንቋ ከተሠራበት የምርምር ቋንቋ ለመሆን እንደሚችል ቀድሞም ከፍተኛ ተናጋሪ የነበረው እንደነበር የተመሠከረለትም ነው ብለዋል።
የዘዬ ልዩነቶች በሁሉም የሚዲያ፣ የትምህርትና የሥራ በሆኑ የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ቋንቋዎች የሚስተዋል እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አማረ መንገሻ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የግል ጤና ተቋማት ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው ተገቢ ግልጋሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ
አሊያንስ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቀ
በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመጡ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዉ መቀጠል ይኖርባቸዋል – የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ