የገና ሰሞን በጉራጌ !!!

የገና ሰሞን በጉራጌ !!!

በየዓመቱ ገና በመጣ ቁጥር በልዩ ድምቀት የሚከወን ባህላዊ የሴቶች ጨዋታ ”ኢምር…ኢምር” ይባላል። ትርጉሙም ፀሐይ …..ፀሐይ…. እንደማለት ነው።

የጉራጌ ብሔረሰብ ቱባ ባህሎች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ገና በመጣ ቁጥር በየዓመቱ ከሚከናወኑ ባህላዊ ስርአቶች መካከል በብሔረሰቡ ቋንቋ ”ኢምር…ኢምር” ይባላል። ስያሜውም ፀሐይ ፀሐይ እንደማለት ነው።

ይህ ድንቅ የሴቶች በዓል በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በየዓመቱ በገና ዕለት ሴቶች በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል።

በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ቡኢ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወሪ/ት አበባ ከበደ እና ወ/ሮ ብርቄ ንጉሴ አንደሚሉት የገና እለት በማለዳው ቀሚስ ለባሽ ልጃገረዶች ”ኤጎስቴ”(ጓዴ/አብሮ አደጌ ) እያሉ ተጠራርተው ከበሮ፣ ጠላ: በቅቤ የታሸ ቆሎና ድፎ ዳቦ ይዘው ይሰባሰባሉ።

የናፍቆት ሰላምታና ዝግጅታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ምስራቅ ዞረው እግራቸውን ዘርግተው በመደዳ በመቀመጥ ከቻሉ በቁጥራቸው ልክ ወንፊት ይይዛሉ ካልቻሉም በእድሜ ታላቋ በመያዝ ቀጣዩ ተግባር ፀሃይዋን በወንፊቱ ቀዳዳ እያዩ ”ኢምር ኢምር #አት…ኢምር ኢምር #ኪት ” እያሉ እስከ 12 መቁጠር ስርአቱን ይከናወናል።

ልጃገረዶቹ ይህንን ካደረጉ በኋላ ቆሎው፣ ጠላው እና ዳቦውን ከወንፊቱ ስር አድርገው፦

”ኢምር ኢምር ቦግ ቤል…ኢምር ቦግ ቤል

ዬዳኮኛ ኧቡር ተክ ቤል”…እያሉ ይጫወታሉ።

”ፀሀይ ሆይ ፈካ በይ

የእናታችን ጠላት ዱብ በይ” እንደማለት ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

በምስራቅ ጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ተካ ኢሚር ኢሚር የሶዶ-ክስታኔ ቤተ ጉራጌ በድምቀት ከሚያከብራቸው በአላት መካከል መሆኑን ገልፀው ከዚሁ ጎንለጎን በሰፊ መስክ(አንቃት) ሲጫወቱ ያረፋፈዱት ወንዶቹ ደግሞ የገና ዱላቸውን ከፍ አድርገው ”እንዞሪቴ” የተሰኘውን ጨዋታ እየጨፈሩ ወደ መንደር ይመጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።

”ዬ ዬ እንዞሪቴ ገና ነበቦ

ምድር ሰማይ ጠበቦ”

ጌታችን በመወለዱ ደስታ በምድር መብዛቱን ለማመላከት የሚዘፈን መሆኑን አውስተው ይህም እየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ወርቅ፣ ከርቤ እና እጣን በእጅ መንሻነት ይዘው በኮከብ እየተመሩ ከምስራቅ የመጡትን ”ሰብአ-ሰገል” የሚያስታውስ ነው ብለዋል።

ኢምር ኢምር ከጨዋታ ጎን ለጎን አብሮ መብላትና መጠጣት እንደሆነ ገልፀው ይህም ለወጣቶች ፍቅር እና አንድነት እንዲኖር ያስችላል ሲሉ ሃላፊው ገልፀዋል።

ማህበረሰቡ ያሉትን ቱባ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲቀጥል ሃላፊነቱ እንዲወጣ ጠቁመው የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ከሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ኢሚር ኢሚር በቀጣይ አመት በሁሉም አከባቢዎች እንደሚከበር አቶ ጌታቸው አመላክተዋል።

ዘጋቢ : ፍስሃ ክፍሌ- ከወልቂጤ ጣቢያችን