ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግና በማዘመን የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ገለፀ።
በዞኑ ኮቾሬ ወረዳ የጭንጨስ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት ይፋዊ የምስረታ መርሐግብር በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ታሪኩ፥ የወረዳው አስተዳደር ከንግግር ባለፈ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎችን በተግባር እየመለሰ መሆኑን ጠቁመው፥ አዲስ የተመሠረተው ማዘጋጃ ቤት በሚያደርጋቸው ልማታዊ ሥራዎች ጎን በመሆን በማንኛውም ልማታዊ ሥራዎች ላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የነቃ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡ ሲያነሳ የነበረውን የመዋቅር ጥያቄ መመለሱን የገለጹት አስተዳዳሪው፥ አሁንም ያልተመለሱ የመንገድ፣ የመብራት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ መሠረተ ልማቶችን ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን እውን ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተደጋግፈንና ተጋግዘን ከሠራን የማናስመዘግበው ድል የለም ያሉት አስተዳዳሪው፥ ህብረተሰቡ መንግሥት ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያወርዳቸው መመሪያዎችንና መዋቅሮችን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ረድኤት ክፍሌ፥ ከተሞችን በማስፋፋትና በማልማት ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በማዘመን የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ መምሪያው እየሠራ መሆኑን ገልፀው፥ የሐንቁና የባያ ቀበሌ ነዋሪዎች ማዘጋጃው እንዲመሠሰረት ላሳዩት ተነሳሽነት አመስግነዋል።
ሕብረተሰቡ አካባቢውን ለማልማት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እጅጉን የሚበረታታ መሆኑን በማስታወስ ማዘጋጃ ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሠራሮችን መከተል እንደሚገባ ኃላፊው አስገንዝበዋል።
የወረዳው ከተማና መሠረተ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ገመደ የገጠር ቀበሌያትን ወደ ከተማነት በማልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ አንዱ ሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን በመጠቆም የከተማ መስፋፋት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ መንግስት በዘርፉ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ኃላፊው የጭንጨስ ታዳጊ ማዘጋጃ ልማት ከከተማው ነዋሪዎች አልፎ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ አዋሳኝ አካባቢ ነዋሪዎችን በልማትና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቁመው ለጋራ ጥቅም በጋራ የመቆም ባህልን የሚያጎለብት መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ወርቁ በየነ፣ ወ/ሮ ጽጌ ጅክሶ እና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት በወረዳው እየተመዘገበ ባለው ልማት መደሰታቸውንና አድናቆታቸውን ገልጸው ከወረዳው አስተዳደር ጋር በልማትና መሠል ተግባራት በጋራ ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የገና ሰሞን በጉራጌ !!!
የወልቂጤ ከተማ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች ህብረት ከወልቂጤ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የገናን በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ
በጎፋ ዞን የላሃ ከተማ አሰተዳደር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርቷል